“ፀሐይ፡ የኢትዮጵያ አቪዬሽን አጀማመር” በሚል ርእስ የተዘጋጀ መጽሐፍ በደማቅ ሥነሥርዓት ተመረቀ

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በካፕቴን ዘላለም አንዳርጌ የተዘጋጀውን እና “ፀሐይ የኢትዮጵያ አቪዬሽን አጀማመር”  በሚል ርእስ ያሳተመውን መጽሐፍ ሚያዚያ 15 ቀን 2013 ዓ ም በአካዳሚው ቅጥር ግቢ በደማቅ ሁኔታ አስመርቋል፡፡

በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ፕ/ር ባህሩ ዘውዴና ዶ/ር  አሉላ  ፓንክረስት  ስለመጽሐፉ ታሪካዊና ቅርሳዊ አንድምታ ዳሰሳቸውን አካፍለዋል፡፡

አንጋፋ ባለሞያዎች ይህ 346 ገጽ ያለው መጽሐፍ ኢትዮጵያ የጥንታዊ  ሥልጣኔ አሻራ ባለቤት ብቻ ሳትሆን፣ በዘመናዊውም  ሥልጣኔ ቀደምት መገለጫ የሆነውን አውሮፕላንን በመሥራትም ከቀዳሚዎቹ የዓለማችን አገራት ተርታ የምትሰለፍ መሆኗንም ማብሰሩን አድንቀዋል፡፡

በውስጡ የአቪዬሽን አጀማመር ታሪካችንን፣ በኢትዮጵያውያን ሞያተኞች ተሳትፎ ፀሐይ የተሰኘች አውሮፕላን መሠራቷንና በጣሊያን ወረራ ወቅት በጣሊያኖች ተወስዳ አሁን በሮም እንደምትገኝ ጭምርም በሰፊው ይገልጻል፡፡

የመጽሐፉ ምርቃት መጽሐፉን ከማስተዋወቅ ባሻገር፣ በአሁኑ ወቅት በጣሊያን አገር የምትገኘውን ‹ፀሐይ› አውሮፕላን ወደ አገር ቤት በቅርስነት ለማስመለስ ለሚካሄደው ጥረት ግብኣት የሚሆኑ ሃሳቦች በስፋት የተንጸባረቁበት ነበር፡፡

(የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ምረቃውን በተመለከተ የሰጡትን ሽፋን ይህንን በመጫን ያገኛሉ)