የጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ጋር በትብብር በሚስሩባቸዉ ጉዳዮች ላይ መከሩ፡፡

በኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ የተመራ ልኡካን ቡድን የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ዋና መሥሪያ ቤትን ጎብኝቷል።

በአካዳሚው ጽ/ቤት በተካሄደው የሁለቱ ተቋማት የሥራ ሓላፊዎች ውይይት ላይ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጽጌ ገብረ-ማርያም አካዳሚው ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ስላከናወናቸው እና እያከናወናቸው ስላላቸው ተግባራት፣ ዋና ዋና የሥራ መርሃ ግብሮች፣  ዓላማዎች እና የተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ ሰፊ ገለጻ አድርገዋል።

ከገለጻው በኋላ በተካሄደው ውይይት ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ከአካዳሚው ጋር ለመሥራት የሚችልባቸው ሰፋፊ መስኮች መኖራቸው የተነሣ ሲሆን፤ በሁለቱም ወገን አብሮ ለመሥራትም ያለውን ፍላጎት መሠረት አድርጎ እና በትብብር የሚሠራባቸውን ዘርፎች የለየ  የመግባቢያ ሰነድ ለመፈራረም ተስማምተዋል።

ዶክተር ሊያ የአካዳሚውን የሳይንስ ማእከል የተለያዩ ኤግዚቢቶችን እና የሥራ እንቅስቃሴዎችን ተዘዋውረው ከተመለከቱ በኋላ አካዳሚው የሳይንስ እውቀትና ባህልን በማኸዘብ የኢትዮጵያን ሕዝቦች  የልማት ምኞቶችን ለማሳካት ሳይንሳዊ እውቀትን እና ፈጠራን የሚያጎለብትበትን ተቋም በመጎብኘታቸው ትልቅ ደስታ እንደተሰማቸው በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል።

አካዳሚው ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በማስረጃ የተደገፉ ምክረ ሐሳቦችን ለመንግሥት በመስጠትና የኅብረተሰቡን የሳይንስ ግንዛቤ በማሳደግ ረገድ  የተመዘገቡት ውጤቶች ተስፋ ሰጭ ጅምር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አካዳሚው ከጤና ሚኒስቴር ጋር ያለውን ትብብር በማጠናከር በሀገሪቱ በጤናው ዘርፍ  የተሻለ ውጤት  እንጠባበቃለን ሲሉ በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው ገልጸዋል።

በጉብኝቱ ላይ ከጤና ሚኒስቴር በኩል የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ፣ የአርማወር ሐንሰን የምርምር ተቋም ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ እና ሌሎችም ከፍተኛ የሥራ ሓላፊዎች የተገኙ ሲሆን፤ የአካዳሚውን የሳይንስ እና የሥነ ጥበባት ማዕከላት ጎብኝተዋል፤ አካዳሚው ስላሳተማቸው የምርምር ደረጃቸውን የተበቁ የኅትመት ውጤቶችም ገለጻ ተደርጎላቸዋል፡፡