የክቡር ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ መታሰቢያ ሐውልት ምርቃትና ሙያዊ ውይይት መርሐ ግብር ተካሄደ

በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ስም የተሰየመው የሥነ ጥበባት ማዕከል ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመተባበር የእውቁን ደራሲ፣ ዲፕሎማት እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የነበሩትን የክቡር ብላቴን ጌታ ኅሩይ መታሰቢያ ሐውልት ምርቃት እና ሙያዊ የውይይት መርሐ ግብር አካሂዷል።

የሐውልት ምርቃት መርሐ ግብሩ ከመከናወኑ ቀደም ብሎ መስከረም 5 ቀን 2016 ዓ.ም የክቡር ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴን 85ኛ የእረፍት መታሰቢያ በማስመልከት በአካዳሚው ቅጥር ግቢ ውስጥ በተሰናዳው  ሙያዊ የውይይት መድረክ ላይነባሩና አዲሱ  የባህል ፍልሚያ በኅሩይ ወልደ ሥላሴ ሥራዎች ላይ በተሰኘ ርእስ የውይይት መነሻ ሃሳብ በዶክተር እንዳለ ጌታ ከበደ ቀርቦ ሙያዊ ውይይት ተከናውኗል።

በውይይቱም ላይ በርካታ የኪነ- ጥበብ ባለሙያዎች እና የጥበብ አፍቃሪያን ተገኝተው የዝግጅቱ ተሳታፊ ሆነዋል። ዶክተር እንዳለጌታ ደራሲው የ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ የኢትዮጵያ ዘመናዊ የሥነ ጽሑፍ ጅማሮ ላይ ስላነሷቸው ማኅበረ-ባኅል ርዕሰ ጉዳዮች በስፋት ትንታኔ ሰጥተውበታል፡፡ አክለውም የኅሩይ ወልደ ሥላሴን ማንነነት እና የአስተሳሰብ መንገድ፣ የአጠቃላይ መጽሐፎቻቸው ይዘትና ትኩረት እንዲሁም የባህል ምንነት እና ፋይዳ ላይ ሙያዊ ትንተና አቅርበዋል።

የኅሩይ የልጅ ልጃቸው ወይዘሮ እምዬ ተክለ ማርያም በመታሰቢያ ሐውልቱ ምረቃት መርሐ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ብላቴን ጌታ ኅሩይ ለሀገራቸው ሁለንተናዊ ሥልጣኔና ዕድገት መሻሻል ጥለው ያለፉት አሻራ በትውልድ ዘንድ አበርክቷቸው ሲታወሱ እንዲኖሩ ለስማቸው ማስታወሻ የሚሆኑ ተግባራትን እያከናወኑ የሚገኙ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚና ሌሎች አካላትንም አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ በበኩላቸው አካዳሚው በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 የሚገኘውን የሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ስመጥር ጸሐፊ እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ መኖሪያ ቤት እና ግቢን ተረክቦ የቀድሞው ይዞታውን ሳይለቅ እያለማ እየተገለገለበት እንዳለና በዚኽ ታሪካዊ ህንፃ ውስጥም በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ሥም የሥነ ጥበባት ማዕከልን በማቋቋም የተለያዩ የሥነ ጥበባት ዘርፎችን በሳይንሳዊ መንገድ የማዘመን ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

አንጋፋው የታሪክ ተመራማሪ ኤምሬተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ በመርሐ ግብሩ ላይ ባቀረቡት ገለጻ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ በአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባነት፣ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርነት፣ በቀይ መስቀል፣ በውጭ ዜጎችን የሚዳኝ ልዩ ፍርድ ቤት፣ በኢትዮጵያ ባንክ አስተዳደር ምክር ቤት ውስጥ በፕሬዝዳንትነት፣ ከ20 በላይ መጻሕፍትንም በማሳተም ለሀገር ልማት ያገለገሉ ሲሆን ኢትዮጵያ ወደ ሊግ ኦፍ ኔሽንስ (League of Nations) ስትቀላቀል ልዑክ በመሆንም በመጨረሻም በኢጣሊያ ስትወረር አቤቱታዋን ለማሰማት ከቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ጋር ሰፊ ጥረት ያደረጉ የሀገር ባለውለታ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ኅሩይ በጥንታዊ የሀገር በቀል ዕውቀቶችና በዓለም አቀፋዊ ጉዞና ንባብ የተቀረጹ እንደነበሩም አውስተዋል። ባሕላቸውና ትውፊታቸ ሳይበረዝ የሰለጠኑ ሀገራትን ስልጣኔና መልካም ልምዶችን ለመቅሰም ካላቸው ጉጉት የተነሣ አዲስ አበባ በሚገኘው የስዊድን ሚሽን ትምህርት ቤት ገብተው የእንግሊዝኛ ቋንቋ መማራቸውንም ጠቅሰዋል። ከእንግሊዝኛ በተጨማሪም የዐረብኛ ቋንቋን ለማጥናት ጀምረው እንደነበር ፕሮፌሰር ባህሩ ተናግረዋል፡፡

እኝኽ የሀገር ባለውለታ በኢጣሊያ ወረራ ምክንያት በ1931 ዓ.ም በስደት በነበሩበት እንግሊዝ ሀገር አርፈው በ1940 ወደ እናት ሀገራቸው አስክሬናቸው መጥቶ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንዲያርፍ ቢደረግም እስከአሁን ምንም አይነት መታሰቢያ ሐውልት ስላልነበራቸው የሥራቸው አድናቂ እና አክባሪዎች እርሳቸውን ለመዘከር የሚያስችል ምልክት እንዲኖር ሲያስታውሱ ቆይተዋል፡፡

በዚኽም መሰረት በቤተሰቦቻቸው እና በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ አስተባባሪነት ከ85 ዓመት በኋላ አካላቸው የሀገራቸውን አፈር እንዲለብስ በማድረግ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር የሥራቸው አድናቂዎች እና አክባሪዎች እንዲሁም ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት የመታሰቢያ ሐውልታቸው ምርቃት መርሐ ግብር ማክሰኞ መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡00 በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተናውኗል።

ድረ ገጽ፦ https://eas-et.org/

ፌስቡክ፡- (20+) Facebook

ዩትዩብ:- https://www.youtube.com/results?search_query=ethiopian+academy+of+science

ሊንክድኢን፦ (21) Ethiopian Academy of Sciences: Overview | LinkedIn

ትዊተር፦ https://t.co/QCEJk0jXKB