የኢትዮጵያ የሥርዓተ ፆታ መማማሪያ መድረክ በጎንደር ዩኒቨርስቲ ዓውደ ጥናት ተካሂዷል

በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሥር የተደራጀው የኢትዮጵያ የሥርዓተ ፆታ መማማሪያ መድረክ“ በጎንደር ዩኒቨርስቲ ዓውደ ጥናት ተካሂዷል፡፡

 

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ከዓለም አቀፍ ሣይንስን የማምጠቅና ፖሊሲ መረብ /International Network for Advancing Science and Policy (INASP)/ ከተሰኘና ተቀማጭነቱ ለንደን ከሆነው ድርጅት ጋር በመተባበር “የሥርዓተ ፆታ አሸናፊዎች ዓውደ ጥናት /Gender Champions Workshop/” በሚል ርዕስ ከግንቦት 16 – 18 /2014 ዓ.ም. በጎንደር ዩኒቨርስቲ አስተናጋጅነት አካሂዷል፡፡

በዓውደ ጥናቱ በአማራና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ከሚገኙ 9 ዩኒቨርሰቲዎችና 3 የምርምር ተቋማት የተውጣጡ 25 ከፍተኛ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ሲሆን የጎንደር ዩኒቨርሰቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ካሳሁን ተገኝ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር አስጀምረዋል፡፡

በንግግራቸውም የሴቶችን ሁለንተናዊ አቅም በመገንባት በትምህርት፣ በምርምር፣በቴክኖሎጂ ልማትና ሽግግር እንቅስቃሴዎች የላቀ ተሳትፎ ኢንዲያበረክቱ ማስቻል የሁሉም ተቋማት አገራዊ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመቀጠልም የጎንደር ዩኒቨርሰቲ ለሴት መምህራን ልዩ ትኩረት በመስጠት ከመማር ማስተማሩ በተጨማሪ በምርምር፣ በማህበረሰብ አገልግሎቶችና በቴክኖሎጅ ሽግግር ሥራዎች ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ተግቶ እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

ዓውደ ጥናቱን በንግግር የከፈቱት የአካዳሚዉ ሥራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ በበይነ መረብ ባደረጉት ንግግር የሥርዓተ ፆታ መማማሪያ ፎሬም የተቋቋመበትን ዋና ዓላማ፣ የወደፊት ግቦችንና የሥርዓተ ፆታ እኩልነትና ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ በአካዳሚዉ በመከናወን ላይ ያሉትን ተግባራት ጠቁመዋል፡፡

በተለይም በከፍተኛ ባለሙያዎች ተነሳሽነት ለተመሰረተው የሥርዓተ ፆታ መማማሪያ መድረክ ድጋፍ በመስጠት በከፍተኛ የትምህርት እና በምርምር ተቋማት የሥርዓተ ፆታ እኩልነትንና ተጠቃሚነትን ለማስፋፋት የሚያግዙ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በዓውደ ጥናቱ የኢትዮጵያ ሴት ምሁራን በጥናትና ምርምር ስራዎች ያላቸውን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራትን በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ ፎረሞች አለመኖራቸው የፈጠረውን ክፍተት በማንሳት የተቋቋመው መድረክ ንቁ ተሳታፊ በመሆን ክፍተቱን ለመሙላት ስለሚቻልበት ተወያይተዋል።

ይህንን አካሄድ በዩኒቨርስቲዎች፣ በምርምር ተቋማት ውስጥ ለማስፋፋት ስለሚቻልበትም የጋራ አቅጣጫ እንደሚለይና የሥራ ዕቅድ እንደሚነደፍ ተሳታዎች ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሥርዓተ ፆታ መማማሪያ መድረክ እና በአካዳሚው ትብብር ካሁን በፊት ሁለት ተመሳሳይ ዓውደ ጥናቶች በአርባ ምንጭና በአርሲ ዩኒቨርስቲዎች የተካሄዱ ሲሆን ሦስተኛው ደግሞ በጎንደር ዩኒቨርስቲ ትብብርና አስተናጋጅነት ለሦስት ቀናት ተካሂዷል፡፡

በዓውደ ጥናቱ ማጠቃለያ አስተያየታቸውን የሰጡ ተሳታፊዎች በነበራቸው ቆይታ በርካታ ልምዶችንና መልካም ተሞክሮዎችን ማግኘታቸውን ገልጸው ወደየተቋሞቻቸው ሲመለሱ ሊተግብሯቸው የሚገቡ ተግባራትን እንዲያቅዱ በመደረጉም ስራቸውን ወዲያውኑ እንደሚጀምሩ ገልፀው ለጎንደር ዩኒቨርሲቲና ለኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ በመጨረሻም ለተሳታፊዎችና አዘጋጆች የእውቅና ምስክር ወረቀት ተበርክቶ መርሀግብሩ ተጠናቋል፡፡