የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የግብርና ሥራ ቡድን ከግብርና ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ጋር መከረ

የሥራ ቡድኑ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከግብርና ምርምር እና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት እንዲሁም ከተለያዩ  ተቋማት  ከተወጣጡ  የዘርፉ ከፍተኛ ባለሙያዎች ጋር የመከረበትን መርሐ ግብር አካሂዷል።

የመርሐ ግብሩ ዓላማ የሥራ ቡድኑ አባላትን ተሳትፎ በማሳደግ፣ የግብርናውን ዘርፍ ማነቆዎች በጥናት በመለየት ዘላቂ መፍትሔ ማበጀት፣ በባለ ድርሻ አካላት የተጀመሩ ግብርናን ትራንስፎርም የማድረግ ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ምሁራን አዋጭ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ከፖሊሲ ዝግጅት ጀምሮ  እስከ ትግበራ አዳዲስ  ሐሳቦችን  በማምጣት  የድርሻቸውን እንዲጫወቱ ስትራቴጂያዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር መሆኑን የመድረኩ አወያይ ዶክተር ሙሉጌታ መኩሪያ አብራርተዋል።

መርሐ ግብሩን በንግግር የከፈቱት የሥራ ቡድኑ ሊቀመንበር ዶክተር ጌታቸው ገብሩ የሥራ ቡድኑ የአባላቱን ተሳትፎ በማጎልበት ከተለያዩ ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊና ሀገራዊ መንግሥታዊ ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት በማሳደግ የአካዳሚውን ሀገራዊ ተልዕኮዎች ለማሳካት እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

 የውይይቱ  ተሳታፊዎችም በግብርና ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ከመሠረቱ  ለመፍታት መወሰድ ያለባቸውን የመፍትሄ ሐሳቦች በማቅረብ በንቃት እንዲሳተፉ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩቱ ለሥራ ቡድኑ ጽሕፈት ቤት በቅጥር ግቢው ማመቻቸቱ አባላቱ የምርምር ሥራዎችን ከተቋሙ ጋር በቅርበት እየተናበቡ እንዲሠሩ ከማስቻሉ በላይ፣ ተቋማዊ ስትራቴጂያዊ ግንኙነትን የሚያጠናክር መሆኑን ገልፀው ኢንስቲትዩቱን አመስግነዋል።

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና መሥሪያ ቤት ቅጥር ግቢ በተካሄደው መርሐ ግብር ላይ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የሥራ ኃላፊዎች፣ ሌሎች በግብርናው ዘርፍ የሚሠሩ የተለያዩ የመንግሥት ፖሊሲ አውጪዎች እና የግብርና ተመራማሪዎች ተገኝተዋል።

በዕለቱ “የግብርና ትራንስፎርሜሽን በኢትዮጵያ፡ የባለሙያዎች ኅብረት ሚና” በተሰኘ ርዕስ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሤ ሙያዊ ገለጻ አድርገው ውይይት ተካሂዷል።

የግብርና ምርምር ሥርዓትን ማሻሻል በሚያስችሉ እና  ውጤታማ በሚያደርጉ የኤክስቴንሽን፣ የገበያ ትስስር፣ የኢንዱስትሪ ሥርዓት የመሳሰሉ ጉዳዮች ለግብርና ትራንስፎርሜሽን ወሳኝ መሆናቸውን ዶክተር ማንደፍሮ ገልጸዋል።

የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶ አደሮች አሠራር በማዘመን ተጠቃሚ ለማድረግ ከተጀመረና ውጤት ከተገኘበት ፕሮግራም ውስጥ የግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ክላስተር ተጠቃሹ መሆኑን በመርሐ ግብሩ ላይ አብራርተዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ተገኝተው ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ፣በኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ በኋላቀር አሠራር እንዳይቀጥል  መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ገልጸው፤ ለሀገራዊ የልማት ግቦች ስኬት ሙያዊ ድጋፍ በመስጠት ምሁራን  የአንበሳውን ድርሻ  እንዲወጡ ጥሪ  አቅርበዋል።

አያይዘውም፣ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሀገራዊ ጠቀሜታ ባላቸው ጉዳዮች ላይ ጥናቶችን የሚያደርግና በማስረጃ የተደገፈ የፖሊሲ ምክረ ሐሳብ ለመንግሥትና ለባለድርሻ አካላት ለመስጠት የተቋቋመና ከፍተኛ ምሑራንን በአባልነት ያቀፈ እንደመሆኑ መጠን፣ ለሀገር የሚጠቅሙ ጥናቶችን በማቅረብ መንግሥትን እንዲያግዝ ጠይቀዋል።

የግብርና ሚኒስቴር የእርሻና ሆርቲካልቸር ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር መለስ መኮንን በበኩላቸው፣ በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በጥናት መለየቱንና የመፍትሔ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን አንስተው፤ ወደተሻለው ደረጃ ለማድረስ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከሳይንስ አካዳሚ ጋር ተቀናጅቶ የመሥራት ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል።

ከተለያዩ ተቋማት የተወጣጡ የዘርፉ ከፍተኛ ምሁራንና ባለሙያዎች በዘርፉ የተገኙ ውጤቶችንና ማነቆዎችን አንስተው ውይይት አድርገዋል።

የኢትዮጵያን ግብርና በተለያዩ ጊዜያት ለማሻሻልና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተወሰዱ የመፍትሔ አቅጣጫዎችና እርምጃዎች የሚፈለገውን ውጤት አለማምጣታቸው በውይይቱ ወቅት ተነስቷል።

አጥኚዎችና ተመራማሪዎች ለሀገር ልማት በሚጠቅም የፖሊሲ ዕቅድና ትግበራ ወቅት ከመንግሥት ጋር ተናበው ካልሠሩ፣ ሀገራዊ የልማት ግቦችን ለማሳካት አዳጋች ስለሚሆን፤ በተለያዩ አስተምህሮአዊ ልዩነቶች ላይ ሙያዊ ውይይት በማካሄድ ልዩነቶችን በማስታረቅ ከተግባቡ በኋላ ለፖሊሲ አውጪዎች ጠቃሚ ግብዓት ማቅረብ እንዳለባቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።