የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በሞዴል ተቋምነት የዕውቅና ሰርተፊኬት ተበረከተለት

በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል የተካሄደው 5ኛው ‘‘ንባብ ለሕይወት’’ ዓውደ ርዕይ ከሐምሌ 28 ቀን 2014 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 2 ቀን 2014 ዓ.ም ሲካሄድ ቆይቶ  ነሐሴ 7 ቀን 2014 ዓ.ም  በይፋ ተጠናቅቋል።

ዓውደ ርዕዩን ያዘጋጁት የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ከንባብ ለሕይወት ኢትዮጵያ ጋር በመቀናጀት ነው።

በዝግጅቱ ላይ ከ200 በላይ የመጻሕፍትና የምርምር ተቋማት የሳተፉ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ጎብኚዎች መሳተፋቸውን አዘጋጆቹ ገልጸዋል።

የኢትዮጵየ ሳይንስ አካዳሚ ሳይንሳዊ ባህልና ፈጠራን ለማበረታታት አካዳሚያዊ መጻሕፍትንና የምርምር መጽሔቶችን አሳትሞ የሚያሰራጭ ሲሆን በሳይንስ ማዕከሉ አማካኝነት የፈጠራና የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን ለማስተማሪያነት መጠቀም እንዲሁም ሥነጥበባትን በሳይንሳዊ መንገድ ማጎልበትን እያከናወነ ይገኛል፡፡ 

ከነዚህም መካከል በዓውደ ርዕዩ ላይ የአካዳሚ ፕሬስ ራሱን በማስተዋወቅ መጻሕፍቱን አሰራጭቷል፤ የሳይንስ ማዕከሉ የፊዚክስ ኤግዚቢቶችን በማሳየት ወጣቶችን እና ጎልማሶችን አነሳስቷል፤ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነ ጥበባት ማዕከልም ተግባራቱን የማሳወቅና የአካዳሚው ቡድን የአካዳሚውን አጠቃላይ አገልግሎቶች በቃል፣ በድምጽና በምስል ዕይታ በማስተዋውቁ በአዘጋጅ ኮሚቴው ተመርጦ በሞዴል ተቋምነት የዕውቅና ሰርተፊኬት ተበርክቶለታል። በዓውደ ርዕዩ መዝጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚን ጨምሮ ከተሳተፉት የመጻሕፍትና የምርምር ተቋማት መካከል በዘርፉ ጉልህ አስተዋጽዖ ላበረከቱት የዕውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።