የስዕል አውደ ርዕይ መዝጊያ ሥነ ሥርዓት

የዕውቁ ሰዓሊ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የስዕል ትርዒት መጋቢት 30 2014 . በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነጥበባት ማዕከል አዘጋጅነት ተከፍቶ ለአንድ ሳምንት በደማቅ ሁኔታ ሲጎበኝ ቆይቶ በደማቅ ሥነ ሥርዓት ተቋጭቷል።

ትርዒቱን በርካታ ሰዎች ሲጎበኙ ከቆዩ በኋላ ባሳለፍነው ቅዳሜ ሚያዝያ 8 ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ በተከናወነው የመዝጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ የሰዓሊ አፈወርቅ ተክሌን ሙያዊ እና ሰዋዊ ማንነት ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡

የስዕል አውደ ርዕይ የሰዓሊውን 10ኛ ዓመት የእረፍት መታሰቢያን በማስመልከት የተዘጋጀ ሲሆን፣ ሰዓሊው በሕይወት ሳሉ በክብር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም እንዲቀመጡ ከሰጧቸው ሥራዎቻቸው መካከል የተመረጡ 22ቱ የቀረቡበት ነበር፡፡ ከስዕሎቹ በተጨማሪ ሰዓሊው ለስዕል ሥራቸው ይጠቀሙባቸው የነበሩ ብሩሾች እና የተጀመሩ ቀለሞች በትርዒቱ ላይ ለዕይታ ቀርበዋል።

በርካታ የሥነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የሰዓሊው አድናቂዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በተከናወነው የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጽጌ ገብረማርያም እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ሀገራችን ካፈራቻቸው እና ሥማቸው ገናና ከሆኑ ሠዓሊያን መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን አስታውሰዋል።

አያይዘውም አንኮበር ከተሰኘች ገጠር ከተማ ተወልደው ዓለም አቀፋዊ ለመሆን የበቁ፣ በሥራቸውም የሀገር ፍቅርን፣ የአብሮ መኖርን እና ሌሎች መልካም እሴቶችን አግዝፈው ለማሳየት ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ ባለሙያ መሆናቸውንም ፕሮፈሰር ጽጌ አብራርተዋል፡፡

በተመሳሳይ የአካዳሚው የሥነ ጥበብ ዘርፍ የሥራ ቡድን ሰብሳቢ ሰዓሊና ቀራፂ አቶ በቀለ መኮንን እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በሥራቸው ሙያቸውን ያስከበሩ ጠቢብ መሆናቸውን እና በዚህ ያህል ስፋት በሀገር ውስጥ ስዕሎቻቸው ለህዝብ በይፋ ሲታይ ከብዙ ዓመታት ወዲህ የመጀመሪያው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በስዕል ትርዒቱ ላይ ከ1950ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ በአብስትራክት፣ በከፊል አብስትራክት፣ በእውናዊ እና በንድፍ ደረጃ የተሠሩ ታዋቂና ከዚህ በፊት ለዕይታ ቀርበው የማያውቁ ሥራዎች እንደ ተካተቱበት አብራርተዋል፡፡

በመዝጊያ ሥነ ሥራዓቱ ላይ በሠዓሊ በቀለ መኮንን አጋፋሪነት የተመራ በሰዓሊ አፈወርቅ ህይወት እና ሥራዎች ላይ ያተኮረ ውይይት የተካሄደ ሲሆን በዚህ ሙያዊ ውይይት ላይ የሰዓሊው የረዥም ዘመን የቅርብ ጓደኛ የነበሩት ደራሲ አያልነህ ሙላት የሰዓሊውን ሰዋዊ ተክለ ሥብዕና ላይ የውይይት መነሻ ያቀረቡ ሲሆን ሙያዊ መልካቸው ላይም ሰዓሊ ጌታ መኮንን ሀሳቡን አጋርቷል።

ሎሬቱ በሕይወት ሳሉ የእኔን ሥራ የሚያዩ ሁሉ ተስፋ እንዲያገኙ፣ ስለኢትዮጵያ እና ስለ አፍሪካ ጥሩ ስሜት እንዲሰማቸው፣ የፀሐይን ጮራ እንዲሞቁ፣ ከሁሉም በላይ ግን “ይቻላል” የሚል እምነት እንዲኖራቸው ፍላጎታቸው እንደሆነ ደራሲና ሃያሲ አያልነህ ሙላት ገልጸዋል።

በውይይቱ በቅርብ የሚያውቋቸው በርካታ አንጋፋ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የተገኙ ሲሆን፣ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ እንደ ኢትዮጵያዊ ምሁርና የጥበብ ሰው በጥንታዊት ኢትዮጵያ ታሪክ፣ ነጻነት፣ ባሕልና ሥልጣኔን በእጅጉ የሚኮሩ ብቻ ሳይሆኑ ጠንቅቀውም የሚያውቁ የታሪክ ሰውና ቅርስ ጠባቂ ሰው እንደነበሩ አስረድተዋል።

በቀረቡት ሐሳቦች ላይ በመመርኮዝም ሰፊ ውይይቶች የተደረገ ሲሆን የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የሥነጥበባት ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ይታገሱ ጌትነትም ለዝግጅቱ ስኬት ጉልህ ሚና የተጫወቱ ተቋማትና ግለሰቦችን አመስግነው የዚህ አይነት ሙያዊ ውይይቶች በየአስራ አምስት ቀኑ በቀጣይነት እንደሚከናወኑ በማስታወስ ዝክረ አፈወርቅ ተክሌ የሥዕል ትርዒትና የውይይት መርሃ ግብር በሥኬት መጠናቀቁን አስተአውቀዋል፡፡

 

More links:

Fana TV

 
Nahoo TV
 
Addis TV
 
EBS TV

https://www.youtube.com/watch?v=DQv2-rWRQ_I

 
Reporter Newspaper 
 
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ 10ኛ ዓመት የእረፍት መታሰቢያ የስዕል ትርዒትን ካታሎግ

የሚቀጥለውን ማስፈንጠሪያ በመጫን ይመልከቱ::