የመሠረታዊ የሥነጽሑፍ የክረምት ወራት ሰልጣኞች የስልጠና ማጠናቀቂያ መርሐግብር ተከናወነ

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የሥነጥበባት ማዕከል፣ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ለሁለት ወራት ለሚያዘጋጀው የክረምት የሥነጽሑፍ ስልጠና ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቶ ቅዳሜ መስከረም 7 ቀን 2015 ዓ.ም የስልጠና ማጠቃለያ መርሐግብር በአካዳሚው ቅጥር ግቢ  አከናውኗል፡፡ በማጠቃለያ መርሐግብሩ ላይም በሰልጣኞች ልዩ ልዩ ኪነጥበባዊ ዝግጅቶች ቀርበዋል፡፡

የደራስያን ማኅበሩ ላለፉት 10 ዓመታት ሲያከናወን የቆየው የሥነጽሑፍ ስልጠና ለሁለት ዓመታት በኮቪድ ወረርሺኝ ምክንያት ተቋረጦ ከቆየ በኋላ የዘንድሮው ስልጠና ሲከናወን ለ8ኛው ዙር ሲሆን የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነጥበባት ማዕከል ለስልጠናው መሳካት ከ2009 ዓ.ም አንስቶ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱ ተገልጿል።

የስልጠናው ዓላማ ተተኪ ወጣቶችን በሥነ ጥበባት ሙያ ዘርፎች ከማብቃት ባሻገር በልምድ እና ፍላጎት የሚጽፉ ደራስያንንም አቅም ማጎልበት ነው፡፡ ቀደም ሲል በተካሄዱ ስልጠናዎች በርካታ ሰልጣኞችን ማሰልጠን የተቻለ ሲሆን በ2014 ዓ.ም የክረምት ወራት ከ75 በላይ ሰልጣኞች ስልጠናቸውን ተከታትለው አጠናቀዋል፡፡

ስልጠናው ሙሉ በሙሉ በከፍተኛ የዘርፉ ባለሙያዎች ለ80 ሰዓታት የተሰጠ ሲሆን ጎን ለጎን ከ48 ሰዓታት በላይ በተዛማጅ የሥነጥበብ እና ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ወርክሾፕና ገለጻ ተከናውኖበታል፡፡ በተጨማሪም አንጋፋ ደራስያን እየተገኙ ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡

የደራስያን ማኅበር ከተቋቋመበት መሠረታዊ ዓላማዎች አንዱ ተተኪ ጸሐፍያን ማፍራት ሲሆን በየዓመቱ ስልጠና መስጠቱም የተነሳበትን ዋና ዓላማ ለማሳካት እንደሆነ የኢትዮጵያ ደራሲያን  የማኅበር ፕሬዚዳንት ደራሲ አበረ አዳሙ በመርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል።

ስልጠናው የተሳካ እንዲሆንም የኢትዮጵያ ቤተመዛግብት እና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ እና ሰላም ኢትዮጵያ ሰፊ ድጋፍ በማድረጋቸው የደራሲያን ማኅበሩ ፕሬዚዳንት ደራሲ አበረ አዳሙ ምስጋና አቅርበዋል።

ማኅበሩ በዘንድሮው ክረምት በመሠረታዊ የሥነ ጽሑፍ ትምህርት ላሰለጠናቸው ሰልጣኞች እና ለስልጠናው ስኬት ድጋፍ ላደረጉ አካላት የምሥክርና የእውቅና  ሰርቴፊኬት አበርክቶላቸዋል።

በስልጠናው ማጠቃለያ መርሐግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ ባስተላለፉት መልዕክት ተተኪ ወጣቶች ስልጠናውን እንደ መሸጋገሪያ ተጠቅመው በሳል ድርሰቶችን በመጻፍ ለራሳቸውና ለሀገራቸው እንዲተርፉ አሳስበዋል።