ወጣቶች በቴክኖሎጂ ዘርፍ እውቀትና ክህሎቱ ኖሯቸው አዳዲስና ችግር ፈቺ የፈጠራ ውጤቶችን እንዲያበረክቱ እየተደረገ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ከስቴም ፓወር ጋር በመተባበር በ2017 ዓ.ም. የክረምት ወቅት ለ6ኛ ዙር ለሦስት ተከታታይ ወራት በኤሌክትሮኒክስና በኮምፒዩተር ሳይንስ መስኮች በንድፈ ሐሳብና በተግባር ላሰለጠናቸው 27 ሴት እና 10 ወንድ፤ በአጠቃላይ ለ37 ተማሪዎች የስልጠና የምስክር ወረቀትና ለፈጠራ ሥራቸው እውቅና የመስጠት መርሐግብር የተማሪዎቹ ወላጆችና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት አካሄዷል።

ተማሪዎቹ የንድፈ ሐሳብና የተግባር ስልጠና ከተከታተሉ በኋላ በ13 ቡድኖች ተከፍለው የተለያዩ ችግር ፈቺ ያሏቸውን የፕሮጀክት ውጤቶች (Prototypes) ሠርተው ማቅረባቸውን የአካዳሚው የሳይንስ ማእከል ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ መስፍን እንግዳወርቅ አሳውቀዋል።

ከ13 ፕሮጀክቶች መካከል ቀዳሚ ደረጃን ያገኘው የፈጠራ ሥራ የአካባቢ አየርንና የመልክዓ ምድር አቀማመጥ እንዲሁም የአፈሩን ለምነት ሁኔታ ቴክኖሎጂው ተገንዝቦ ምን ዓይነት ተክል ቢተከል እንደሚያዋጣው ለአምራቹ ትክክለኛ መረጃ ይሰጣል። በተጨማሪም አንድ ተክል በበሽታ ሲጠቃ ቅድመ መረጃ መስጠትና ተገቢ እርምጃ እንዲወሰድ የሚያሳውቅ የፈጠራ ሥራ ሲሆን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ግምገማ መሰረት አንደኛ ደረጃን አግኝቷል።

ሁለተኛው የፈጠራ ሥራ ተንቀሳቃሽ አስተማሪ ሮቦት ሲሆን ከተለመደው አስተማሪነት የሚለየው የተለያዩ ትምህርቶችን በብዙ ቋንቋዎች ማስተማር የሚችል ነው።

ሦስተኛው የንብ ቀፎና የእህል ጎተራ ጎን ለጎን አጣምሮ የያዘ ቴክኖሎጂ ሲሆን የንብ ቀፎው ለንቦቹ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ንቦቹ ምርታማ እንዲሆኑና ምንም ዓይነት ችግር ቢደርስባቸው ለአናቢው በገመድ አልባ የመገናኛ መሣሪያ አማካይነት የሚያስውቅ ነው። በተጨማሪም ጎተራው ለሚከማቸው እህል አመቺ ሁኔታ በመፍጠር እህሉ ሳይበላሽ እንዲቆይ የሚያስችል የፈጠራ ሥራ ነው።

አራተኛው የፈጠራ ሥራ ለውጊያ አገልግሎት የሚውል ተሽከርካሪ ሮቦት (ታንክ) ሲሆን ሮቦቱን የሚያንቀሳቅሰው ሰው የመተኮስ እርምጃ የሚወስደው ከቪዲዮ ካሜራ ትክክለኛ መረጃ ሲያገኝ ብቻ ነው።

በመርሐግብሩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአካዳሚው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር በላይ ካሳ አካዳሚው ሳይንስን ለማሕዘብ በርካታ ተግባራትን እንደሚያከናውን ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ሳይንሳዊ አሠራሮችን ለማጎልበትና የፈጠራ ሥራዎችን ለማበረታት በሳይንስ ማእከሉ ስር በሚገኙ የSTEM ማእከላት በአዲስ አበባ ከሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለተወጣጡ የፈጠራ ሥራ ዝንባሌ ያላቸውና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች በየዓመቱ በክረምት ወራት የሚሰጠው በንድፈ ሐሳብና በተግባር የተደገፈ ሥልጠና አንዱ መሆኑን አብራርተዋል። 

የቴክኖሎጂ ሀሳቦችን ከማላመድ ባሻገር ተማሪዎቹ ያስተዋሏቸውን አካባቢያዊና የማኅብረሰቡን ችግሮች ለመቅረፍ ያሳዩትን ተነሳሽነት አድንቀው አካዳሚው የፈጠራ ሥራን ለማበረታታት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ ምህንድስናና ሂሳብ (STEM) ስልጠና ክፍሎች በውስጣቸው ባሉ የተሟሉ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችና ኮምፒውተሮች አማካኝነት የመማር ማስተማር ሥራዎችን ከንድፈ ሐሳብ ተኮር ወደ ተግባራዊ የፈጠራ ሥራ እንዲያተኩሩ ስቴም ፓዎር በመላው ሀገሪቱ እያስተባበረ መሆኑን በክብር እንግድነት ተገኝተው ንግግር ያደረጉት STEMpower Inc. ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶ/ር ስሜነው ቀስቅስ አስረድተዋል።

የሚሰጠው ድጋፍ የፈጠራ ችሎታና ዝንባሌ ያላቸው ተማሪዎች በንድፈ ሐሳብ ያገኙትን ትምህርት በተግባር እንዲለማመዱ ለማድረግ፣ በዘርፉ ልምድ ባካበቱ ባለሙያዎች ሙያዊ ድጋፍ እንዲያገኙ፣ ወጣቶች በራስ መተማመን አቅማቸውን እንዲያጎለብቱና በአሳታፊ የሳይንስና ስተም ማእከላት እንዲሰለጥኑ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም የዓለም ሀገራት ከድህነት ተላቀው ወደ እድገት የተሸጋገሩት ለSTEM ትምህርትና ፈጠራ ሥራዎች ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው በመሥራታቸው መሆኑን አስረድተው ሁሉም ባለድረሻ አካላት የምርምርና ፈጠራ ሥራዎችን መደገፍ እንደሚገባቸው መልእክት አስተላልፈዋል።

የአካዳሚው ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ በመዝጊያ ንግግራቸው የፈጠራ ሥራዎች የውድድሩ ዓላማ የሳይንስ እና የፈጠራ ሥራዎችን ለማበረታታት እና ተማሪዎች የፈጠራ ችሎታቸውን አውጥተው በመሥራት ራሳቸውንና ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ ለማስቻል መሆኑን ጠቁመው ለዚህ ዓላማ ስኬት የአካዳሚው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ተማሪዎቹ ለፈጠራ ሥራዎቻቸው በአነሳሽ ምክንያት ከጠቀሷቸው መካከል ዋነኛው በአካባቢያቸው ላስተዋሏቸው ችግሮች መፍትሔ ለማስገኘት እንደሆነ አስረድተዋል።

ይህንንም አካዳሚው ከመደበኛ ትምህርታቸው በተጓዳኝ ሥራ ፈጣሪ ሆነው እንዲወጡ ከስቴም ፓወር ጋር በመቀናጀት ባደረገላቸው ድጋፍ ችግር ፈቺ የሆኑ አዳዲስ ፈጠራዎችን መሥራት እንደቻሉ ገልጸዋል።

ተማሪዎች ያጎለበቷቸውን የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎች ለወላጆችና ለተጋባዥ እንግዶች የማስጎብኘትና በመጨረሻም ለተማሪዎቹም እውቅና የመስጠት መርሐግብር በአካዳሚው ዋና ጽ/ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ቅዳሜ ጥቅምት 1 ቀን 2018 ዓ.ም ተካሂዷል።