የገጠር ትራንስፎርሜሽን ለኢትዮጵያ መዋቅራዊ ሽግግር ያለው ፋይዳ በምሁራን ተመከረ

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ወቅታዊና ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታን ከግምት ውስጥ በማስገባት “የገጠር ትራንስፎርሜሽን በኢትዮጵያ: ከግብርና ወደ መዋቅራዊ ሽግግር ትልም” በሚል ርዕስ የምሁራንና የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል። በዚህ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂና ቢልት ኢንቫይሮመንት ኮሌጅ በተካሄደው የገለጻና ውይይት መድረክ ላይ የግብርና አመራሮች፣ ባለሙያዎች፣ የፖሊሲ አጥኚዎች፣ ተመራማሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በአካልና በበይነ መረብ ተሳትፈዋል።

በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት (ATI) ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ማንደፍሮ ንጉሴ ሰፊ ገለጻ ያቀረቡ ሲሆን፤ የገጠር ትራንስፎርሜሽን ለኢትዮጵያ አጠቃላይ መዋቅራዊና ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ዋነኛው መተላለፊያ መንገድ መሆኑን ገልጸዋል።

የውይይት መድረኩን በአወያይነት የመሩት የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር በላይ ካሳ፣ አሳታፊ ሀገራዊ እድገትን ለማምጣት የገጠር ትራንስፎርሜሽን መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። አካዳሚው ይህንን ርዕስ የመረጠው ወቅታዊና ስልታዊ ጠቀሜታ ስላለው መሆኑን የጠቀሱት ፕሮፌሰር በላይ፣ ውይይቱ የሀገሪቱን የልማት አቅጣጫ በተመለከተ በማስረጃ ላይ የተመሰረተ ምክክር ለማድረግ ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።

ዶ/ር ማንደፍሮ በገለጻቸው  የገጠር ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ትኩረት ሊያደርግባቸው የሚገቡ ዋና ዋና ነጥቦችን ሲዘርዝሩ የተቀናጀ የገጠር መሰረተ-ልማትና አገልግሎቶችን ማስፋፋት፣ በግብርናውና በሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች መካከል ያለውን ትስስር ማጠናከር፣ ለግብርና እድገት ድጋፍ የሚሰጡና የከተማ-ገጠር ትስስርን የሚያሳልጡ ከእርሻ ውጭ ያሉ (Non-farm) የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን ማበረታታት እና ጠንካራ ተቋማትን መገንባት፣ አሳታፊ የፋይናንስ ስርዓት መዘርጋትና የገጠሩን ማህበረሰብ የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል መሆናቸውን አብራርተዋል።

የግብርና ትራንስፎርሜሽን ለገጠርም ሆነ ለመዋቅራዊ ሽግግር መሰረት መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ማንደፍሮ ተገቢው ሽግግር የሚመጣው አርሶ አደሩ ለራስ ፍጆታ ብቻ ከሚያመርትበት የአሰራር ዘይቤ ወጥቶ ለገበያ የሚተርፍ ምርት ማምረት ሲችል መሆኑን አብራርተዋል። ይህም ለገጠር መሰረተ ልማት መስፋፋት ማለትም ለኤሌክትሪክ፣ ለመስኖ፣ ለመጋዘን፣ ለምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች፣ ለመንገድና ለዲጂታል ትስስር መጠናከር ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል።

ዶ/ር ማንደፍሮ የገጠር ትራንስፎርሜሽን ምሰሶዎችን ሲዘረዝሩ፦ ገበያ ተኮር ግብርና፣ የገጠር ፋይናንስ፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ ማህበራዊ ልማትና ጠንካራ ተቋማት፣ ሰላማዊ አብሮ መኖር አብራርተዋል።

በመድረኩ ላይ የተሳተፉ ምሁራንና ባለድርሻ አካላት በሀገሪቱ ሰላም ማስፈን ለገጠር ትራንስፎርሜሽን ስኬት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን በአጽንኦት አሳስበዋል። ሰላም በሌለበት ሁኔታ የልማት ሥራዎችን በዘላቂነት ማከናወን እንደማይቻል ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል።

በመጨረሻም ዶ/ር ማንደፍሮ የኢትዮጵያ የሳይንስ ማህበረሰብ በማስረጃ ላይ የተመሰረቱ የልማት ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ ረገድ የላቀ ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ አቅርበዋል። ይህም በውጭ እርዳታ ላይ ያለንን ጥገኝነት በመቀነስ፣ በራስ መተማመን ላይ የተገነባና የማይበገር ኢኮኖሚ ለመፍጠር እንደሚረዳ ገልጸዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየትና ባቀረቧቸው ጥያቄዎች፣ የኢትዮጵያን የገጠር ማህበረሰብ ለመለወጥና የግብርናውን ዘርፍ የወደፊት እጣ ፈንታ ለማሳመር ሰላምን ማረጋገጥ የጋራ ጥረት፣ ሳይንስ፣ ፈጠራና በምርምር ላይ የተመሰረቱ መፍትሄዎች ወሳኝ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የአካዳሚው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር በላይ በመድረኩ በአካልና በበይነ-መረብ ለተሳተፉ አካላት ምስጋናቸውን ገልጸው  መርሐ-ግብሩ ወደፊትም የሚቀጥል በመሆኑ ተሳታፊዎች ንቁ ተሳትፏቸውን እንዲቀጥሉ በማሳሰብ የዕለቱን የውይይት መርሐ-ግብር መጠናቀቁን በመግለጽ አጠናቀዋል።