የግብርና ምርምር ሥርዓት መሪው የዶ/ር ስሜ ደበላ የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ተመረቀ

በገስጥ ተጫኔ ተጽፎ የኢትዮጵያ አካዳሚ ፕሬስ ያሳተመው “ስሜ ደበላ፡ የታላቁ የግብርና ምርምር ሥርዓት መሪ’’ የተሰኘ የዶ/ር ስሜ ደበላን አበርክቶዎች የሚዘክር የሕይወትታሪክ መጽሐፍ ቅዳሜ መጋቢት 6 ቀን 2ዐ17ዓ.ም. በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በኅሩይ አዳራሽ ቤተሰቦቻቸው፣ ጓደኞቻቸው እና የሙያ አጋሮቻቸው በተገኙበት ተመርቋል፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ በርካታ የግብርና ሳይንስና ከሌሎች የሙያ ዘርፎች የተውጣጡ ከፍተኛ ዕውቀትና ልምድ ያካበቱ አንጋፋና ወጣት ባለሙያዎች ተሳትፈዋል። በዕለቱ መጽሐፉ የዶ/ር ስሜ የሕይወት ታሪክ ብቻ ሳይሆን ያኖሩት አሻራ የኢትዮጵያን ግብርና ለማዘመን የሚያግዙ ሳይንሳዊ ፈለጎችና ራዕያቸው ለሀገራችን ልማትና ለህዝባችን ኑሮ መሻሻል ያደረጓቸውን ጥረቶች የሚያሳይ መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የግብርና ሥራ ቡድን ሊቀመንበር ዶ/ር ጌታቸው ገብሩ በመርሐግብሩ መግቢያ ባደረጉት ንግግር የዶ/ር ስሜን ህይወቱንና ሥራውን ስንዘክር ከሙያዊ ስኬቱ ባሻገር መልካም ስብዕናው፣ ታማኝነቱ ፣ ባለራዕይ እና በልበ-ሙሉነት የሚሠራ ታላቅ ሰው መሆኑን አውስተዋል።

ዛሬ ሁላችንም የእሱን ሥራዎች የምናንፀባርቅበት ፣ ትውስታችንን የምናጋራበት እና በጥልቅ አምኖበት ይሠራ የነበረውን ተግባራት ለማስቀጠል ያለንን ቁርጠኝነት የምናድስበትቀን ነው ብለዋል። ዶክተር ጌታቸው አያይዘው የዛሬውን ሁነት ትርጉም ያለውና የሚታወስ እንዲሆን ላደረገው ቁርጠኝነት የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚን አመስግነዋል።

በመርሐግብሩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአካዳሚው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር በላይ ካሳ ዶ/ር ስሜ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ መሥራች እና ለኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ሥርዓት እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ታላቅ ሰው መሆናቸውን መስክረዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕ/ር ንጉሴ ደቻሳ በበኩላቸው፣ ዶ/ር ስሜ ደበላ መሪ ብቻ ሳይሆኑ የኢትዮጵያን የግብርና ሥነ ምህዳር በምርምር ለመቀየር ደከመኝ፣ ሰለቸኝ፣ ሳይሉ የሠሩና የተሟገቱ ፋና ወጊ እንደነበሩ ተናግረዋል።

ፕሮፌሰር ንጉሴ የዶ/ር ስሜ ደበላን አመራር አወድሰው፣ ኢንስቲትዩቱ በእርሳቸው መሪነት በሰብልና እንስሳት እርባታ፣ በአፈር ጥበቃ እና በውሃ አያያዝ እያስመዘገበ ያለውን ውጤት አሻሽለው እንደሚያስቀጥሉ አብራርተዋል።

በዚህ በፕሬሱ፣ በአካዳሚው የግብርና ዘርፍ ሥራ ቡድን እና በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት እንዲሁም በባለታሪኩ ቤተሰብ ትብብር በተዘጋጀው የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የዶ/ር ስሜ የሙያ አጋሮች እና ወዳጆቻቸው የባለታሪኩን አስተዋጽኦዎች የሚገልፁ ምስክርነቶችን የሰጡ ሲሆን በኪነጥበብ ባለሙያዎችም ከመጽሐፉ የተመረጡ ክፍሎች ተነበዋል፡፡