“እረኛዬ” በተሰኘው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ ሙያዊ ውይይት ተካሄደ

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የሥነጥበባት ማዕከል “እረኛዬ” በተሰኘው ተከታታይ  የቴሌቪዥን ድራማ ዙሪያ ሙያዊ  የውይይት መድረክ አካሒዷል።

በዝግጅቱ ላይ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር ሰሎሞን ተሾመ ከፎክሎር አንጻር ድራማውን የቃኙባቸውንነጥቦች አቅርበዋል፡፡ በትንታኔያቸውም ላይ፣ ይህ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ የታሪክ አወቃቀሩ፣ የገፀባህሪዎቹ አመራረጥ፣ የትወና ብቃት፣ የቦታ አመራረጥ፣ ዳይሬክቲንግ፣ ቀረፃው የሙያውን ደረጃ ከፍ ያደረገና የአገራችንን የፊልም ገፅታ የቀየረ እንደሆነ ዶክተር ሰለሞን ገልጸዋል።

የድራማው አዘጋጅና ደራሲ ቅድስት ይልማ እና ደራሲዎቹ አዜብ ወርቁ እና ቤዛ ኃይሉ በመድረክ ላይ ተሰይመው ስለድራማው አጠቃላይ ይዘት እና ቀጣይ ዕቅዳቸውን ለታዳምያን አካፍለዋል። በዚህ ወቅት ድራማው የአገራችንን ባህል፣ ሥነልቦና፣  ትውፊቶችንና እሴቶችን የተላበሰና ሳቢ እንዲሆን በማድረግ  ትውልድን ከባህል ብረዛና ከማንነት ቀውስ ለመታደግ ታልሞ እንደተሠራ ገልጸዋል።

በድራማው በትወናና በሌሎች ሥራዎች የተሳተፉ አካላት ሐሳባቸውን ያካፈሉ ሲሆን፤  በውይይቱ የተጋበዙ የዘርፉ ባለሙያዎች እና ተማሪዎችም ገለጻዎቹን ተከትሎ በተካሔደው ውይይት ላይ ተሳትፈዋል፡፡

እነዚሁ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ድራማው የበርካታ ተመልካቾችን ቀልብ የሳበ፣ በትርጉም ከሚቀርቡ የውጭ አገር ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች አይናችንን ወደ አገርኛ የመለሰ ተከታታይ ድራማ ነው ሲሉ ገልጸውታል። ድራማው ከሰፊ ማኅበራዊ ጠቀሜታው ባሻገር  ጉልህ ፖለቲካዊ ፋይዳ እንዳለውም  ተጠቁሟል።

በውይይት መድረኩ “ጉንጉን’’ እና ‘’የወዲያነሽ’’ በተሰኙ ተወዳጅ የልቦለድ ድርሰቶቻቸው የሚታወቁት እና በዚሁ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ አብዬ በቃሉ  ሆነው በመተወን ተወዳጅነትን ያተረፉት ደራሲ ኃይለ መለኮት መዋዕል እና በእማማ ቸርነት የተወከለች ተዋናይት ድርብወርቅ ሰይፉ በድራማው ላይ ስለነበራቸው ተሳትፎ አብራርተዋል፡፡

በሙያዊ ውይይት መድረኩ ማጠቃለያ ላይ የድራማው ደራሲና ዳይሬክተር ቅድስት ይልማ በርካታ ተመልካቾች የድራማው ቀጣይ ክፍሎች መቼ እንደሚጀምር በጉጉት ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ የሰጡ ሲሆን የድራማው ቀጣይ ክፍሎች ቀረጻ ተጠናቆ ቅንብር ላይ እንደሚገኝና በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ማለትም ግንቦት መጨረሻ ወይም ሰኔ መጀመሪያ ለዕይታ እንደሚበቃ አሳውቀዋል።