የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራንና ተማሪዎች ለአገር ዕድገት ያላቸው ሚና ከአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ተመክሮ በመነሳት ጥቅምት 30/2010 ዓ.ም ሐሙስ ከ11፡00 ሠዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (5 ኪሎ) ግቢ በሚገኘው አዳራሽ በፕ/ር ባሕሩ ዘውዴ መርሐ-ግብር መሪነት በዶ/ር ወርቁ ነጋሽ ገለፃ ቀርቦ በምሁራን ውይይት ተደረገ፡፡
በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ድህረ-ምረቃ ት/ት ቤት በተባባሪ ፕሮፌሰርነት እየሠሩ የሚገኙት ዶ/ር ወርቁ ነጋሽ እንደገለፁት በካሊፎርኒያ ግዛት ያሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጥቅሉ አራት አበይት የውስጥ አካላትን ያቅፋሉ፡፡ እነርሱም ተማሪዎች፣ መምህራን፣ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችና እና የአስተዳር አካላት ናቸው፡፡ ከላይ የተገለፁት አካላት በተለያዩ አገራት የየራሳቸው ጉልህ ሚና እና ተግባር ቢኖራቸውም፤ በታሪክ ዑደት በዓለማችንም ሆነ በኢትዮጵያ በአገር ግንባታ ውጣውረድ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን #የአንበሳውን ሚና$ ይይዛሉ ብለዋል፡፡
በተያያዥነት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሦስት ቁልፍ ተልዕኮዎችን ማለትም የመማር ማስተማር፣ የምርምርና ፈጠራ እንዲሁም የሕብረተሰብ ግልጋሎት/ኃላፊነት (የማሕበረሰብ አገልግሎት) ሥራዎችን እንዲፈፅሙ ይጠበቃል፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ተልዕኮዎች መሠረታዊ ቢሆኑም፤ በዕለቱ ገለፃ ዶ/ር ወርቁ አብይ ትኩረት የሰጡት ጉዳይ አንድ ህብረተሰብ በእድገት ሂደቱ ወቅት ችግሮች ሲገጥሙት የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ሁኔታውን ተረድተው አስተሳብን የመምራትና የማስተካከል ግዴታቸው ላይ ነበር፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መልካም ስብዕናን የተላበሱ ዜጎችን ማፍራታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በሌሎች አገራዊ ተግባራት ላይም ሚናቸው መጉላት ይኖርበታል፡፡ በአገራዊ ዕሴቶች፣ ብዝሐነት፣ ዴሞክራሲያዊ እሳቤዎች፣ ሰብአዊ መብቶች፣ ነጻነቶች/መብቶች፣ መቻቻል፣ ዓለም አቀፋዊ ተግባራትና ኃላፊነቶች፣ ፍትህ፣ ብሔራዊ/አገራዊ ማንነት፣ ሰብዓዊ ክብር እና የመሳሰሉቱን ጉዳዮች አትኩሮት በመስጠት ከህብረተሰቡ ጎን መሰለፍ ግዴታቸው እንደሆነም አብራተዋል፡፡
አቅራቢው አክለውም በአሁኑ ወቅት በዓለማችንና በአገራችን የሚስተዋለውን አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ብዥታዎች እየተመለከቱ ዝም ማለት ለምሁራን ይቻላቸዋልን? በማለት ተሳታፊዎችን ለውይይት ጋብዘዋል፡፡ በውይይቱም አብዛኞቱ ተሳታፊዎች ዝም ማለት እንደማይቻልና በተለያዩ ወቅቶች ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አንስተው አላሠራ ያሉ ማነቆዎችንም ዘርዝረው መክረዋል፡፡ አስቻይ ሁኔታ ያለመኖር፣ አብዛኛው የአገሪቱ ምሁር በእለት ሕይወቱ ውጣውረድ የተጠመደ መሆኑ እንዲሁም ከምርምርና አገራዊ ሁኔታዎችን በላቀ ምሁራዊ ስብዕና ተባብሮ ለማቃናት ከመሞከር ይልቅ በዩኒቨርሲቲዎቹ ውስጥ ያሉ የውስጥ አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታ አያሌ ጊዜና ሀብት እንደሚያጠፋ ተሳታፊዎች በተደጋጋሚ አንስተዋል ውይይት አድርገዋል፡፡
በማጠቃለያለያነት አቅራቢው እንዲህ ያለውን ወቅታዊ ርዕሰ-ጉዳይ ለውይይት እንዲበቃ ማድረጉን የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚን አመስግነው #የእያንዳንዳችን ህይወት እጅጉን አጭር ሲሆን፤ አሁን በቀረችን ጥቂት ዘመን አገራችንን ሊጠቅሙ የሚችሉ ማህበራዊ ኃላፊነቶችን እና ግዴታዎችን በመወጣት የህሊና ተጠባባቂዎች ሆነን ልናገለግል ይገባናል$ በማለት አጭር የገመድ ማሳያ ምሳሌን በምሁራን የአገልግሎት ዕድሜ መስሎ በማቅረብ መድረኩ ተጠናቋል::
በውይይቱ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እንዲሳተፍ ጥሪ የተደረገ ሲሆን ከ100 በላይ ልዩ ልዩ ግለሰቦች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራንና ተማሪዎች በስፋት ታዳሚ ሆነዋል፡፡ የሳይንሳዊ ገለፃና ውይይት መርሐ-ግብሩ በየወሩ የመጨረሻው ሐዉስ ከ11፡00 ሠዓት ጀምሮ ይካሄዳል፡፡