ዳኛቸው ወርቁ ማን ነው?

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነጥበባት ማዕከል የደራሲና ገጣሚ  “ዳኛቸው ወርቁ ማን ነው?” በተሰኘ  ርዕስ   የውይይትና  የመታሰቢያ  መርሐ ግብር አካሂዷል፡፡

ማዕከሉ ከአንድ ዓመት በላይ በኮቪድ ወረርሺኝ እና በልዩ ልዩ ምክንያቶች እንቅስቃሴው ተገትቶ የቆየ ሲሆን በዚህ ዓመት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሂዶ በተቀመጠው አዳዲስ የአሠራር ስልቶች የሥራ እንቅስቃሴውን መጀመሩ ተጠቁሟል።

በውይይት መድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአካዳሚው የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባልና አቃቤ ንዋይ አስቴር ጸጋዬ (ዶክተር) የዛሬው መርሃ ግብርም ተቋርጦ የነበረው የማዕከሉ እንቅስቃሴን ተጠናክሮ መጀመሩን የሚያመላክት፣ ሲሆን የታላቁን ደራሲ፣ ገጣሚና መምህር ዳኛቸው ወርቁን ህይወት እና ሥራዎቹን ለማስታወስና ለመዘከር በማሰብ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም ማዕከሉ በሚያከናውናቸው መርሐግብሮች ላይ ፍላጎቱ ያላቸው ሁሉ በመታደም እንደቀድሞው ሁሉ የዕውቀት ማዕዱ ተቋዳሾች እንዲሆኑና በሌሎች መጠነ ሰፊ ጉባኤዎችእና  የፖሊሲ ምክክሮች ላይ የዘርፉ ምሁራን የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

በእለቱ ደራሲ  እንዳለ-ጌታ ከበደ (ዶክተር) ባቀረቡት የዳሰሳ ጽሑፋቸው የደራሲ ዳኛቸው ወርቁ  የአጻጻፍ ስልቱ የአማርኛን ዘመናዊ ልብ ወለድ ወደ ላቀ ደረጃ  ያሳደጉና  የኢትዮጵያን ሥነ ጽሑፍ በዓለም አቀፉ መድረክ ካስተዋወቁ ጥቂት ኢትዮጵያውያን ደራሲያን አንዱ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ደራሲ ዳኛቸው ወርቁ ’’አደፍርስ’’ የተሰኘ ልብ ወለድ ድርሰቱ ጠጣርና ምጡቅ ሐሳቦችን በተከሸነ  ውብ የአጻጻፍ ስልት፥ ከተለመደው  የቋንቋ አጠቃቀም ስልት ለየት ባለ መልኩ  የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ልዕልና ያሳየ መሆኑንም  አስረድተዋል። (“አደፍርስ”) የተሰኘውን የደራሲውን ሥራ በመመርኮዝ ሰፊ ሥነጽሑፋዊ ትንታኔ አድርገዋል፡፡

ሌላው የመድረኩ አቅራቢ ገዛኸኝ ጸጋው (ዶክተር) በበኩላቸው ገጣሚ  ዳኛቸው «እምቧ በሉ ሰዎች» በሚለው የግጥም መድብሉ ውስጥ በተካተቱ ግጥሞቹ ስለሀገሩ ልማትና ዕድገት ተቆርቋሪነቱን የገለጠ ዕውቅ የሥነ ጽሑፍ ምሁር፥ ሐያሲና ተርጓሚ የነበረ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ዳኛቸው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ትምህርት ክፍል    በረዳት መምህርነት እና በመምህርነት በዩኒቨርሲቲው ያገለገለ ሲሆን  በወቅቱ የተማሪዎች የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ በመሳተፍ ከዘመነኞቹ የኮሌጅ ገጣሚዎች ከነኢብሳ ጉተማ  ዮሐንስ አድማሱ፣ መስፍን ሀብተማርያም ወዘተ ጋር  «ወጣቱ ፈላስማ» በመሳሰሉ ግጥሞቹ የለውጥ ሐሳቡን ሲያስተጋባ የነበረ ገጣሚ እንደነበርም አንስተዋል፡፡

ደራሲና ገጣሚ ዳኛችው ወርቁን እንደሰው ማን ነው የሚለውን ጭብጥ ዳኛቸውን በቅርብ ያውቁት የነበሩት ደራሲና ተርጓ ሳህለሥላሴ ብርሃነማርያም ዳኛቸው የሀገሩን ባህልና እሴቶች ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ ለጊዜ ትልቅ ቦታ የሚሰጥ፣ ሥራን ለነገ ማሳደርን የማያውቅ፣ ለውጥ ፈላጊ፣ ሀገር ወዳድ፣ ስለሀገር ኋላ ቀርነት ሁሌ የሚቆረቆር  ተራማጅ አስተሳሰብ ያለው መሆኑን መስከረውለታል።

የዳኛቸው ወርቁ ሌላው ዐቢይ ሥራ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ደርሶት በአፍሪካን ሲሪስ ውስጥ የታተመውና “The Thirteenth Sun” የተሰኘው መጽሐፍ አስታውሰው ተጨማሪ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተጻፈ ልብወለድ ድርሰት እደነበረውና ለኅትመት ከላከው በኋላ እንዳይታተም እንዲቋረጥ ማድረጉን በማውሳት ትዝታቸውን አጋርተዋል።

የአካዳሚው የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነጥበባት ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ይታገሱ ጌትነት የዳኛቸው የህይወት ታሪክ በአጭሩ ያስቃኘ  ጽሑፍ በንባብ አሰምተው ውይይቱ ተጠናቋል።