የተማሪዎች የቴክኖሎጂ ፈጠራ ሥራዎች ውድድር ተካሄደ

በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የሳይንስ ማዕከል ውስጥ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና በኤሌክትሮኒክስ ቤተ ሙከራዎች በተማሪዎች የተሰሩ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ሥራዎች የምርቃትና ሽልማት ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል፡፡

በተግባር ተኮር ሥልጠናው ላይ ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች በፈጠራ ችሎታቸው እና በዝንባሌያቸው የተመረጡ ተማሪዎች በክፍል ውስጥ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ የቀሰሙትን እውቀት ወደ ተግባር እንዲቀይሩና ችግር ፈች ቴክኖሎጂዎችን  የመፍጠር ክህሎታቸውን እንዲያበለፅጉ ከስቴም ፓወር ጋር በመተባበር ለወራት ተግባር ተኮር ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱን የአካዳሚው የሳይንስ ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን በለጠ ገልጸዋል።

ማዕከሉ የልጆች ሳይንስ፣ የፊዚክስ፣ የጂኦሎጂና ፓሊኦ-አንትሮፖሎጂ ክፍሎች እንዳሉት ገልፀው እነዚህ ክፍሎች በውስጣቸው ባሉ አሳታፊ ኤግዚቢቶች አማካኝነት አዝናኝ በሆነ መልኩ ጎብኚዎች ስለ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ እንደሚረዱም ተናግረዋል፡፡

Science Centre director

ሌላው በማዕከሉ ሥር ያለው ክፍል የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ ምህንድስናና ሂሳብ (STEM) ስልጠና ክፍል ሲሆኑ ከተለያዩ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ተማሪዎች በኮምፒዩተር ሳይንስና በኤሌክትሮኒክስ ዘርፎች የሚሰለጥኑበት እንደሆነም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ተማሪዎች የንድፈ ሀሳብና የተግባር ስልጠና ከተከታተሉ በኋላ በቡድን በመሆን በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ባሉ ችግሮች ላይ ያተኮሩ መፍትሄ ሰጪ የፈጠራ ስራዎችን ያከናውናሉ ብለዋል አቶ ወንድወሰን፡፡

በማእከሉ ከመስከረም 24 ቀን አንስቶ ለአንድ ወር ከአስራ አምስት ቀን ባካሄደው ሥልጠና አርባ አንድ ተማሪዎች መሳተፋቸውንና 11 ፕሮጀክቶች ተሰርተው ለውድድር መቅረባቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ከነዚህ መካከል 4 አራቱን ፕሮጀክቶች በቀጣይ በትምህርት ሚኒስቴር አዘጋጅነት በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው 6ተኛው የሳይንስና ምህንድስና ውድድር እንዲቀርቡ መመረጣቸውን ገልጸዋል፡፡

እነዚህ አራት የፈጠራ ሥራዎችም ወደተለያዩ ተቋማት የሚገቡ ተገልጋዮች ማስክ እና ሳኒታይዘር በአግባቡ እንዲጠቀሙ ማስገንዘቢያ  እና ሳኒታይዘር መርጫ ያለው፣ አስቀድሞ የመዘገበውን ፊት በመለየት የቤትና የአጥር በር የሚከፍትና የሚዘጋ፣ በጣት አሻራ የተመሰረተ ሰራተኞች በሥራ ቦታ መገኘታቸውን መቆጣጠር የሚያስችል ፈጠራ እና በጣት አሻራ የመኪና ሞተር ማስነሻና የብሉቱዝ መቆጣጠሪያ ያለው ፈጠራዎች ቀርበዋል፡፡

የእለቱ የክብር እንግዳ የነበሩት የኢትዮጵያ ወጣቶች ሳይንስ አካዳሚ ተባባሪ ሊቀመንበር ዶክተር ብርሃኑ በሻህ በበኩላቸው የውድድሩ ዓላማ የሳይንስ እና የፈጠራ ሥራዎችን ለማበረታታት እና ተማሪዎች የፈጠራ ችሎታቸውን አውጥተው በመሥራት ራሳቸውንና አገራቸውን እንዲጠቅሙ ለማስቻል መሆኑን በዝግጅቱ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል።

አያይዘውም ዛሬ ተማሪዎች ሰርተው ያሳዩአቸው የቴክኖሎጂ ፈጠራ ሥራዎች በፕሮቶታይፕ ደርጃ ያሉ ቢሆኑም ወደፊት የአገሪቱን ችግር ፈች እና የፈጠራ ባለቤቶችን  ወደተሻለ ደረጃ የሚያደርስ ጅምር ሥራ መሆኑን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ  በወጣት ባለሐብትነት ታዋቂ  የሆነውን ‘’አውስቲን ሩሴል’’ የስኬቱ መነሻ በፕሮቶታይፕ ደረጃ ሰርቶ ባሳየው በሰው ሰራሽ ኢንተሌጀንት የሚሰራ የመኪና ሞዴል እንደሆነ አብራርተዋል።

በመሆኑም ተማሪዎች ዛሬ በፕሮቶታይፕ ደረጃ ያሳዩትን የፈጠራ ውጤቶች ወደ አምራችነት ደረጃ ለማሳደግ ሥራቸውን የማስተዋወቅ፣ መማማርና ከኢንዱስትሪዎች ትሥሥር መፍጥር እንዳለባቸው  ዶክተር ብርሃኑ አስገንዝበዋል፡፡

በመቀጠል የተማሪዎቹ ተወካይ ኤልሻዳይ መዝገቡ የሳይንስ አካዳሚዉ በንድፈ ሐሳብ የተማሩትን በተግባር የሚያጤኑባቸው ቤተ ሙከራዎችን ባመቻቸው ሥልጠና ባገኙት ተግባራዊ ልምምድ ወደ ፊት በትምህርታቸውና በሌሎች ሥራዎቻቸው ውጤታማ እንዲሆኑ እንደጠቀማቸው ገልፆ አካዳሚውን አመስግኗል ።

በመርሐ ግብሩ ማጠቃለያ የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እንዲሁም ቡድኖች የተማሪዎች ወላጆች፣ መምህራንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ከሳይንስ አካዳሚው ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።