በሕዝብ ብዛት እና በአገር ዕድገት ትስስር ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት ተካሄደ

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በሥነ ሕዝብ ዕድገትና አጠቃላይ አገራዊ ዕድገት ግንኙነት  እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ገጽለገጽ  እና የበይነ መረብ የውይይት መድረክ ካፒታል ሆቴል አሂዷል፡፡

ሕዳር 10 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ፡- 

የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጽጌ ገብረ-ማርያም በሰጡት ማብራሪያ የሕዝብ ብዛት ለአገር ሀብት መሆኑን ጠቅሰው፤ የሕዝብ ብዛቱ በራሱ ስጋት እንዳይሆን ከምጣኔ ሀብት ዕድገት እናከተፈጥሮ ሀብት ጋር ያለውን ዝምድና በማጣጣም፣ ሥጋትነቱን መከላከል ስለሚያስችሉ ሳይንሳዊ መፍትሔዎች ለመምከር ታልሞ የተዘጋጀ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።

በፍጥነት የሚጨምር የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ከአገራዊ ዕድገት ጋር ተጣጥሞ እንዲሄድ ለማስቻል፣ የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ፣ የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥና የአካባቢ ልማት እንዲፋጠን  ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን በአግባቡ እንዲጫወቱ አካዳሚው ከዴቪድና ሉሳይል ፓካርድ ፋውንዴሽን በተደረገ የገንዘብ ድጋፍ የግንዛቤ ማሳደጊያ የውይይት መድረኮች እያዘጋጀ መሆኑንም ፕሮፌሰር ጽጌ ተናግረዋል።

በመድረኩ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው ንግግር ያረደጉት የኢፌዴሪ የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር  የፖሊሲ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ነመራ ገበየሁ በበኩላቸው፣ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ከፍተኛ የህዝብ ብዛት ላላቸውና በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገሮች እንደዚህ ያለ የምክከር መድረክ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አካዳሚውም የሥነ ሕዝብ ጉዳይ ለሀገሪቱ ዕድገት ወሳኝ መሆኑን በመረዳት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ አመስግነው፣ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ  ፖሊሲዎች፣ ዕቅዶችና አፈጻጸማቸው በመረጃ ላይ የተመሠረቱ እንዲሆኑ ከማድረግ አኳያ አካዳሚው የሚያደርገውን ጥረት ይደግፋል፣ በጋራም ይሠራል ብለዋል፡፡

ውይይቱን የመሩት ዶክተር ሙሉነህ ወልደ ፃድቅ ባደረጉት የመግቢያ ገለጻ፣ በፍጥነት የሚጨምር የሕዝብ ብዛት በአንድ አገር የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ያለው አሉታዊና አዎንታዊ ተጽእኖ ለረጅም ጊዜ አከራካሪ የሆነ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤  በአንደኛው ወገን ያሉ የሥነ ሕዝብና የምጣኔ ሀብት ተሟጋቾች የሕዝብ ብዛት በፍጥነት መጨመር ለአገር ዕድገት እንቅፋት ሊሆን ይችላል ብለው እንደሚከራከሩ እና ሌሎቹ ደግሞ በተቃራኒው ጭመራው ለአገር እድገት ጉልህ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው የሚሟገቱ ስለመሆናቸው በአጭሩ አስተዋውቀዋል፡፡

አያይዘውም በአገሪቱ ውስጥ ያለው አብዛኛው ሕዝብ በእውቀቱና በክሕሎቱ አገልግሎት ሰጪ ወይም አምራች ከመሆን ይልቅ አገልግሎት ፈላጊ ከሆነ የአገር ሀብት በመሆን ፈንታ በአገሪቱ የምርት ሂደት ላይ ተጽዕኖ ሊያመጣ እንደሚችልም ዶክተር ሙሉነህ ገልጸዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ ፕሮፌሰር አሰፋ ኃይለማርያም፣ ዶክተር አለማየሁ ስዩም፣ ዶክተር ግዛቸው በለው እና አቶበላይ አበራ  ከዚህ ከዚህ አንጻር የሕዝብ ብዛት እድገትን የቃኙባቸውን ንግግሮቻቸውን አቅርበዋል፡፡

የሕዝብ ብዛትን እንደ አገር ሀብት መጠቀም የሚቻለው በአገሪቱ ካለው አብዛኛው ሕዝብ  ወቅቱ በሚፈልገው የሳይንስና ቴክኖሎጂ እውቀትና ክሕሎት ብቁ የሆነ አምራችና ሸማች ዜጋ ሲሆን ብቻ  እንደሆነ  በውይይት መድረኩ ላይ  ቁልፍ ንግግር ያደረጉት የምጣኔ ሐብት፣ የሥነ ሕዝብ፣ የኅብረተሰብ ጤና እና የማኅበረሰብ ሳይንስ ምሁራን ገልጸዋል።

በሕዝቦች የዕድሜ መዋቅር ወይም እርከን፣ የውልደትት ምጣኔ  እንዲሁም የሞት ምጣኔ  መቀነስና መጨመር ሊያስከትል የሚችለውን የኢኮኖሚ ዕድገትና ውድቀት ዙሪያም ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የምጣኔ ሐብት እና የሥነ ሕዝብ ከፍተኛ ምሁራን በሰጡት አስተያየት የሕዝብ ቁጥር በፍጥነት መጨመር በዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ ዕድገት ላይ የሚያመጣው አሉታዊ ውጤት መኖሩን ገልጸው፣ ነገር ግን አሉታዊ ውጤቱን ለመቀነስ እያደገ ከሚመጣው ሕዝብ ብዛት ውስጥ አምራች የሆነውን ኃይል በመጨመር ወደ አዎንታዊ ውጤት መቀየር እንደሚቻል  ጠቁመዋል፡፡

አምራች የሆነውን ኃይል በመጨመርና ምቹ የሥራ ከባቢን በመፍጠር ቁጠባንና ኢንቨስትመንት በማሳደግ የሕዝብ ብዛት ሊያስከትለው የሚችለውን ተግዳሮት ወደ መልካም አጋጣሚ መቀየር እንደሚቻልም  ባለሙያዎቹ  ገልጸዋል፡፡

ትክክለኛና የተቀናጀ የሥነ ሕዝብና የኢኮኖሚ ዕድገት ፖሊሲ በአግባቡ ካልተተገበረ  የአምራችነት የዕድሜ ደረጃ ድርሻን ብቻ ማሳደግ የሥነ ሕዝባዊ ትሩፋት ተጠቃሚነትን ለማግኘት የሚያበቃ ዋስትና ሊሆን አይችልም ያሉት የዘርፉ ምሁራን እንዲያውም ለወጣቱ ምቹ ሁኔታ ካልተፈጠረ ሥራ አጥነትን፣ ስደት እና አለመረጋጋትም በመፍጠር በገራዊ ልማት እድገት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊፈጥር ይችላል በማለት ሙያዊ ትንታኔ ሰጥተዋል፡፡

የአካዳሚው ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር የዓለም ፀሀይ መኮንን እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ በውይይቱ መዝጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር በውይይቱ የተነሱ ምክረ ሐሳቦች ለሥነ ሕዝብና ለምጣኔ ሀብት ፖሊሲ ግብዓት የሚያስገኙና የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ  የሚያግዙ መሆናቸውን ጠቅሰው  ለዚህ ሥራ ሥኬት ጉልህ ሚና የተጫወቱትን ዴቪድና ሉሳይል ፓካርድ ፋውንዴሽን እና ሌሎች አካላትን አመስግነዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ ከመንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች፣ ከምርምር፣ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ከልማት  ተቋማት  የተውጣጡ  በሥነ ሕዝብና ልማት ዙሪያ የሚሠሩ፣ በምጣኔ ሀብት፣ በጤና እና በሌሎች የልማት ዘርፎች የተሰማሩ ከፍተኛ ተመራማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

ከታች ያለውን ማስፈንጠሪያ በመጫን  ሙሉውን ፕሮግራም  ይከታተሉ፡፡

ሥነ ሕዝብ ዕድገትና አጠቃላይ አገራዊ ዕድገት ግንኙነት ክፍል 1

 ሥነ ሕዝብ ዕድገትና አጠቃላይ አገራዊ ዕድገት ግንኙነት ክፍል 2

የተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የፓናል ውይይቱን ዘግበው ያሰራጩትን ዘገባ ሊንኮቹን በመጫን ይከታሉ፡-