የመጪው 10 ዓመት አገራዊ የባዮቴክኖሎጂ የምርምርና ልማት ረቂቅ መርሐ ግብር

የመጪው 10 ዓመት አገራዊ የባዮቴክኖሎጂ ምርምርና ልማት ረቂቅ መርግብር ላይ የሚመክር የአንድ ቀን ዓውደ ጥናት ተካሄደ።

ማክሰኞ ጥር 24 ቀን 2014 . አዲስ አበባ

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ከኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በአገራዊ የ10 ዓመታት የባዮቴክኖሎጂ የምርምርና ልማት ረቂቅ መርሐ ግብር ላይ የሚመክር የአንድ ቀን ዓውደ ጥናት አካሄደ፡፡

በዓውደ ጥናቱ ከልዩ ልዩ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል የምርምር ተቋማትና መሥሪያ ቤቶች፣ ከዩኒቨርስቲዎች፣ ከአካዳሚውና ከግሉ ዘርፍ የመጡ ከ50 በላይ ባለሙያዎችና የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

Prof. Tsige Gebre Mariam, Preseident (EAS)

ለዓውደ ጥናቱ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጽጌ ገብረ ማርያም የመርሐ ግብሩ ዋና ዓላማ በእፅዋት፣ በእንስሳት፤ በጤና፣ በኢንዱስትሪና በአካባቢ ባዮቴክኖሎጂ  መስኮች ላይ ያተኮሩ የ10 ዓመት አገራዊ መርሐ ግብሮችን ማዘጋጀት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የኅብረተሰቡ የሳይንስ ግንዛቤ እንዲጎለበት ማገዝ ከአካዳሚው ዓበይት ዓላማዎች አንዱ እንደሆነ ገልጸው፣ ይህንን ለማሳካት የሚያገለግሉ ፕሮግራሞችን ቀርጾ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሠራ እንደሆነም ጠቁመዋል።

አካዳሚው ከኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በቀረበለት ጥያቄ መሠረት የ10 ዓመት አገራዊ የባዮቴክኖሎጂ ምርምር ለልማት መርሐ ግብር (ከ2014 ዓ.ም እስከ 2023 ዓ.ም) ለማዘጋጀት የስምምነት ውል ተፈራርሞ ለሥራው አግባብነት ያለው የትምህርት ዝግጅት እና ልምድ ያላቸውን ከፍተኛ ባለሙያዎች ያቀፈ ቡድን አቋቁሞ ማስጠናቱን እና የመርሐ ግብሩን ረቂቅ ሰነድ ማዘጋጀቱን ፕሬዚዳንቱ አብራርተዋል።

Dr. Bayisa Bedada

ዓውደ ጥናቱን አስመልክተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር  የኢኖቬሽን ልማትና ምርምር ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ባይሳ በዳዳ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ አስተባባሪነት እየተቀረጹ ያሉትና ለውይይት የቀረቡት ረቂቅ መርሐ ግብሮች ኢትዮጵያ የነደፈችው ሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዞ ፈጣን እንዲሆንና ዕድገቱንም ዘላቂ ለማድረግ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አብራርተዋል።

ሁለቱ ተቋማት ተቀናጅተው መርሐ ግብሮቹን ለመቅረጽ ላደረጉት ትብብር አመስግነዋል፡፡አያይዘውም አገራችን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ልማት ረገድ እቅድ በማዘጋጀት ደረጃ የተሻለ እንቅስቃሴ ላይ ብትሆንም በትግበራ ላይ ግን ገና ብዙ መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ ጅምር ሥራው ተጠናቆ የታለመውን ግብ እንዲያሳካ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

በዓውደ ጥናቱ የጥናት ቡድኑ አስተባባሪዎች የሆኑት ፕሮፌሰር እንዳሻው በቀለ  እና  ዶክተር ስዩም ለታ የረቂቅ መርሐ ግብሩን ይዘት በሁለት ክፍል መድበው ገለጻ አድርገዋል፤ በመቀጠልም ውይይት ተደርጎበታል፡፡

Dr Endeshaw Bekele  and Prof. Seyoum Leta (from left to right)

የዓውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የቴክኖሎጂ አቅም የሚለካው ሀገራት ባላቸው የቴክኖሎጂ ቁስ ስብስብ ብቻ ሣይሆን ማኅበረሰቡ ቴክኖሎጂን ለመረዳት፣ ለመጠቀም፣ ለማሻሻልና ብሎም ለመፍጠር አቅም ሲገነባ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ውይይቱን የመሩት የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት  ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ካሳሁን ተስፋዬ እና የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጽጌ ገብረ ማርያም በመሩት ውይይት ላይ፣ የጥናት ቡድኑ አስተባባሪዎችና አባላት ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም ረቂቅ መርሐ ግብሩ  በከፍተኛ ምሁራን የተዘጋጁ በመሆናቸው መላው ኅብረተሰብ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በየዘርፋቸው ትኩረት ሰጥተው ሲተገብሩት  የሚኖረው አገራዊ  ጠቀሜታ ከፍ ያለ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸው፤ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡