እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የሥዕል ትርዒት

በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነጥበባት ማዕከል አዘጋጅነት የእውቁን ሰዓሊ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌን 10 ዓመት የእረፍት መታሰቢያ በማስመልከት እስከ  ሚያዚያ 8 ቀን 2014 . የሚቆይ የስዕል ትርዒት  በይፋ ተመርቆ ተከፍቷል፡፡

ትርዒቱም የአካዳሚው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የአርቲስቱ አድናቂ ባለሙያዎች በተገኙበት ተመርቆ ለጎብኚዎች  በነፃ ክፍት ሆኗል፡፡

ትርዒቱን በእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክትና በመክፈቻ ንግግር ያስጀመሩት የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዘዳንት ፕሮፌሰር ጽጌ ገብረማርያም የዕል  ትርዒቱ የተከፈተው በሥዕል ላይ ያለው ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና፣ ታሪክ፣ አገር በቀል ዕውቀትና ባህል እንዲዳብር መሆኑን ገልፀዋል።

አያይዘውም ‘‘ያለንበት ዘመን ከፍተኛ የማንነት ጥያቄ ውስጥ የገባንበት በመሆኑ ኢትዮጵያዊ ማንነታችንን ለመግለጽ  ዋነኝው መሣሪያ ኪነ ጥበብ ሲሆን እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ሥራዎች ኢትዮጵያዊነታችንን እንድናውቅ ከፍተኛ ዕድል የሚፈጥሩ ናቸው’’ ብለዋል።

አገራችን ኢትዮጵያ ጥንታዊትና ታላቅ አገር መሆኗን ገልጸው ሌሎች ጥንታዊ አገራት  ኪነጥበባቸው፣ ሙዚቃቸው፣ ስዕላቸው ሁሉ ነገር የዳበረው አገር በቀል ዕውቀቶችንና ኪነጥበባትን ከሳይንሳዊ  ዕውቀት ጋር በማዋሃድና በማዘመን  እንደሆነ ፕሮፌሰር ጽጌ አስረድተዋል።

አካዳሚው የሥነ ጥበባት ዘርፍን ይበልጥ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ለማስፋትና ሕዝባዊ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።  

በአካዳሚው የሥነ ጥበባት  የሥራ ቡድን አስተባባሪ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ‘‘አለ’’ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት መምህር፣ ሠዓሊና ቀራፂ አቶ  በቀለ መኮንን ባደረጉት ገለጻ  “የእጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌን  ሥራዎች ትልቅ የጥበብ ልህቀት የሚታይባቸው ናቸው” ብሏል።

በማስከተልም ዛሬ የተከፈተው የሥዕል ትርዒት የሠዓሊው የሥዕል ሥራዎች ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላ በብዛት ለዕይታ የቀረቡበት እንደሆነም ገልጸዋል።