በ ‘‘በዓሉ ግርማ- ቤርሙዳ’’ ቴአትር ዙርያ ሙያዊ ውይይት ተካሄደ”

በውድነህ ክፍሌ ደራሲነት በዶክተር ተሻለ አሰፋ ተዘጋጅቶ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ለእይታ የቀረበው ‘‘በዓሉ ግርማ – ቤርሙዳ’’ በተሰኘ ቴአትር ላይ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የሥነጥበባት ማዕከል አስተአባሪነት ሙያዊ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በቴአትሩ ላይ ሙያዊ መነሻ ሐሳብ በእውቁ አዘጋጅ ተስፋዬ ገብረ ማርያም የቀረበ ሲሆን አዘጋጁ ተሻለ አሰፋ (ዶ/ር) እና ደራሲው ውድነህ ክፍሌ የቴአትሩ የዝግጅት እና የድርሰት ሂደት ላይ ገለጻ እንዲሁም በውይይቱ ተሳታፊዎች ለቀረቡ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ ተሰጥተዋል። ‘‘በዓሉ ግርማ – ቤርሙዳ’’ የደራሲ በዓሉ ግርማ መጨረሻ ላይ ያተኮረና በጥናት እና ምርምር የታገዘ እውነተኛ ታሪክን በምልሰት የሚያስቃኝ ተውኔት ነው። እንደ ተስፋዬ ገ/ማርያም ዕይታም የቴአትሩ አማራጭ ታሪክ (Alternative History)፣ የዘመን ቴአትር (Periodic Theater)፣ በቴአትር ውስጥ ቴአትር (Meta drama) እና በተወሰነ ደረጃ ደግሞ ምርምር-አገዝ ቴአትር (Experimental Theater) እንደሆነ ማሳያዎችን በመጥቀስ አብራርቷል፡፡

በተጨማሪም ቴአትሩ ታሪክን ለመመርመር እንዲሁም የዘመኑን ፖለቲካዊ ትኩሳት በሚዛን ለማየት እድል የሚሰጥ መሆኑን በታዳሚያን ተጠቁሟል፡፡ በውይይቱ ከተነሱ አንኳር ነጥቦች መካከል ቴአትሩ በእውነታና በፈጠራ ሥራ ተቀናጅቶ መሠራቱ የታሪክን እውነታ በግላዊ ተረክ ዕይታ ውስጥ የማሳደር አመክንዮና አከራካሪነቱ፣ የምናብ ዓለም ነዋሪዎች ከተጨባጩ ዓለም ገጸባኅርያት ጋር የተፈጠረ ግንኙነት አሳማኝነት፣ የበአሉ መጨረሻና የቴአትሩ ለበዓሉ ታሪክ ወካይነት፣ እንዲሁም የዝግጅት ቴክኒካዊ እይታዎችና ሌሎች ሌሎች ሙያዊ ነጥቦች ተነስተዋል።በፓናሊስቶችም ሰፊ እና አስተማሪ የሆኑ ምላሾችና አስተያየቶች ቀርበዋል፡፡

በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወ/ሥላሴ የሥነጥበባት ማዕከል በየሳምንቱ የተለያዩ መሰል መርሐግብሮች የሚዘጋጁ ሲሆን የፊታችን ቅዳሜ ነሐሴ 6 2015 ዓ.ም በማዕከሉ አስተባባሪነት በዛጎል መጽሐፍ ባንክ አዘጋጅነት በየ15 ቀኑ የሚሰናዳው “ነገረ መጽሐፍት” ዝግጅት “ሕይወቴ – ለአገሬ ኢትዮጵያ እና ለወገኖቼ ኢትዮጵያውያን ዕድገት የነበረኝ የሥራ ጥማት” በተሰኘው የደጃዝማች ወ/ሰማዕት ገ/ወልድ ግለታሪክ መጽሐፍ ላይ እንዳለ-ጌታ ከበደ (ዶ/ር) ከጸሐፊው ደጃዝማች ወ/ሰማዕት ጋር ቆይታ ያደርጋል።