ፀሐይ፡፡ የኢትዮጵያ አቪየሽን አጀማመር በሚል ርዕስ የተዘጋጀ መጽሐፍ ይመረቃል

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በካፕቴን ዘላለም አንዳርጌ የተዘጋጀውን እና “ፀሐይ፡ የኢትዮጵያ አቪዬሽን አጀማመር” በሚል ርእስ ያሳተመውን መጽሐፍ ሚያዚያ 15 ቀን 2013 ዓ ም ከቀኑ 10 ሰአት ጀምሮ ያስመርቃል፡፡

በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ፕ/ር ባህሩ ዘውዴና ዶ/ር አሉላ ፓንክረስት ስለመጽሐፉ ታሪካዊና ቅርሳዊ አንድምታ ዳሰሳቸውን ያካፍላሉ፡፡

ይህ 346 ገጽ ያለው መጽሐፍ በውስጡ የአቪዬሽን አጀማመር ታሪካችንን፣ በኢትዮጵያውያን ሞያተኞች ተሳትፎ ፀሐይ የተሰኘች አውሮፕላን መሠራቷንና በጣሊያን ወረራ ወቅት በጣሊያኖች ተወስዳ አሁን በሮም እንደምትገኝ ጭምርም በሰፊው ይገልጻል፡፡

የመጽሐፉ ምርቃት መጽሐፉን ከማስተዋወቅ ባሻገር፣ ኢትዮጵያ የጥንታዊ ሥልጣኔ አሻራ ባቤት የሆነች ብቻ ሳትሆን በዘመናዊውም ስልጣኔ ቀደምት መገለጫ የሆነውን አውሮፕላንን በመሥራትም ከቀዳሚዎቹ የዓለማችን አገራት ተርታ የምትሰለፍ መሆኗንም ያበስራል፡፡ በአሁኑ ወቅት በጣሊያን አገር የምትገኘውን ‹ፀሐይ› አውሮፕላን ወደ አገር ቤት በቅርስነት ለማስመለስ ለሚካሄደው ጥረት ምረቃው እንደ እርሾ ሊያገለግል እንደሚችልም ይገመታል፡፡