ጥምቀት ባህል እና ኪነት ሙያዊና ኪናዊ መድረክ

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነ ጥበባት ማዕከል “ጥምቀት፣ ባህል እና ኪነት” በተሰኘ ርዕስ ላይ ሙያዊና ኪናዊ መድረክ አከናወነ፡፡

በተለያዩ አገራት በመዘዋወር የኢትዮጵያን ባህልና ትውፊት ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ እየተጋ ያለው የፈንድቃ ባህል ማዕከል መሥራች አቶ መላኩ በላይ ለዓመታት እያካሄደው ስላለው “ፍለጋ’’ ስለተሰኘው የጥምቀት ፌስቲቫል ፕሮጀክቱ ጉዞ እና በከበራ፣ ባህል እና ኪነት ምንነት ዙርያ ልምዱን ለታዳሚዎች አካፍለዋል፡፡

የጥምቀት በዓል በድምቀቱ እና ውበቱ ከሃይማኖታዊ በዓልነት ባሻገር በተለያዩ ብሔረሰቦች ባህላዊና ትውፊታዊ ክዋኔዎች የተዋበ ክብረ በዓል መሆኑንም አቶ መላኩ አብራርተዋል።

ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ዕድገት ትልቅ ድርሻ ካላቸው በዓላት አንዱና ዋነኛው መሆኑን ጠቅሰው የተባበሩት መንግሥታ የትምህርት፣ የሳይንስና የባህልና ድርጅት (UNESCO) በማይዳሰስ የታሪክ ቅርስነት ጥምቀትን መመዝገቡ ድንበር ተሻጋሪ በዓል አድርጎታል ብለዋል።

በጥምቀት እለት የተለያዩ ብሔረሰቦች በቋንቋቸውና በባህላዊ ውዝዋዜያቸው ምሥጋና ያቀርባሉ ሲል ለአብነት የጋሞ ብሔረሰብ የባህላዊ ኪነት ቡድንን ጠቅሰዋል። በውይይት መድረኩም ላይ የጋሞ ብሔረሰብ አባላት ባህላዊ ልብሶችን በመልበስ የባህሉን ጭፈራ ለታዳሚው አቅርበዋል፡፡

የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነ ጥበባት ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ይታገሱ ጌትነት የመድረኩ መዝጊያ ባደረጉት ንግግር ሐይማኖታዊ እና ባህላዊ ቅርሶቻችን የሀገራችንና የዜጎቻችን መገለጫዎች  በመሆናቸው በማጥናት፣ በመጠበቅ፣ በማሳደግና ለዓለም በማስተዋወቅ ለሀገራችን ልማት እንዲውሉ እናድርግ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡