በአፍሪካ ወጣቶች የባህል፣ የኪነትና የራስን ተረክ በመግለጽ ዙሪያ የልምድ ልውውጥ መርሃግብር ተከናወነ፡፡

በአፍሪካ ወጣቶች የባህል፣ የኪነትና የራስን ተረክ በመግለጽ ዙሪያ የልምድ ልውውጥ መርሃግብር ተከናወነ፡፡  

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነጥበባት ማዕከል የአፍሪካ ወጣቶችን አንድነት ማጠናከሪያ መንገዶች፣ የራስን ታሪክ በራስ መተረክ ለአፍሪካ የነጻነት መንገድ ያለው ድርሻ፣ የባህልና የህዝብ ለህዝብ ትውውቆችን ለማጠናከር የፓናል ውይይት አካሂዷል፡፡

የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ አካዳሚው ወጣት ተመራማሪዎች ሁሉ አቀፍ ልማት ላይ የሚኖራቸውን  ተሳትፎ ለማሳደግና በተሳትፏቸው ልክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል የኢትዮጵያ ወጣቶች ሳይንስ አካዳሚን በማጠናከር ሂደት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም አካዳሚው በየሙያ ዘርፋቸው ምርምርን ጨምሮ የላቀ አስተዋጽዖ ያደረጉትን ምሁራን በየደረጃው አጣርቶ በየዓመቱ በአካዳሚው መደበኛና ተባባሪ አባልነት የሚመርጥ በመሆኑ መሥፈርቱን ማሟላት የሚችሉ ወጣቶች በአባልነት እንዲቀላቀላቀሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ፓን አፍሪካኒዝም አፍሪካውያን እና ትውልደ-አፍሪካውያን አህጉራዊ የጋራጥቅም የሚያስጠብቁበት፤ በራሳቸው ጉዳዮች ላይ ራሳቸው የሚወስኑበት እና የታሪክ ባለቤት በመሆን ራቸው መተረክ የሚችሉበት አካሄድ ሲሆን ለዚህም የአህጉሪቱ ወጣቶች በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልጋቸው ታንዛኒያዊው የማኅበረሰብ አንቂና  የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ  ወጣት ሚካ ቻቫላ አብራርቷል።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ  አፍሪካውያን ወጣቶች ከውጭ ሀገራት ይደርስብናል ያሉትን ጫና እና ያልተገባ ጣልቃ ገብነትን ለመከላከል የፓን አፍሪካኒዝም መርህን ደጋግመው እያነሱ መሆኑን ገልጾ የተለያዩ የአፍሪካ አገራትም በመርሁ ዙርያ ሲተባበሩ ተስተውሏል ብሏል።

አያይዞም”አዲስ አበባ ሁለተኛዋ ቤታችን በመሆኗ በመድናችን ተገኝተን የአፍሪካዊያን ችግር በአፍሪካውያን መፍትሔ ብቻ ለመፍታትና የምዕራባዊያን ሀገራት እና ሚዲያዎቻቸው በአፍሪካ ጉዳይ ላይ የዓልም አቀፍ ስምምነቶችን የጣሰ ጣልቃ ገብነት ለማስቆም ጥረት እያደረግን ነው ብሏል። በማሳያነትም በኢትዮጵያዊያ እና በአፍሪካ ላይ የተቃጣውን የምዕራባውያንን ጫና ለመከላከል የ “No more” ወይም “የበቃ” ዕንቅስቃሴን በይፋ ተቀላቅሎ እየሠራ መሆኑንም አስታውሷል፡፡

በውይይት መድረኩ ተሳታፊ የነበሩት የአፍሪካ ወጣቶች ልማት እና ልህቀት የቦርድ አባል አቶ ዮናስ ወልደሰንበት በበኩላቸው  የአፍሪካ ወጣቶች የአፍሪካን ባህል፣ ጥበብ እና  ቅርስ በመጠበቅ ለትውልድ ማሸጋገር፣ አንድነቷ የተጠናከረ እና የበለጸገች አህጉርን ለመገንባት የማይተካ ሚና እንዳላቸዉ  ገልጸዋል።

በአሁን ወቅት እየተስተዋለ ያለው የአፍሪካውያን የመተባበር እሳቤ ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል ትልቅ እድል ቢሆንም ፓን አፍሪካኒዝም ለችግር ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜ በአፍሪካውያን ሊነሳ እና ሊተገበር የሚገባው መርሕ መሆን እንዳለበት ተሳታፊዎች አስተያየታቸዉን ሰጥተዋል።

የአፍሪካ ባህልጥበባት፣ ባህሎችና ቅርሶች በአፍሪካ አህጉር ውጫዊ ገጽታ ለሚኖረው የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትና አንድነትን ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ተገጿል።

አፍሪካ ዛሬም በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገች ነገር ግን አብዛኛው ሕዝቧ ከድህነት ያልተላቀቀባት  አህጉር ያደረጋት የቅኝ ገዢዎች ከጫኑብን ዘርፈ ብዙ ሳንካዎች ተላቀን፤ ተገቢ ቦታችንንና የራሳችንን እውነተኛ ታሪክ በራሳችን የምንተርክበትና ለአህጉራዊ ጉዳዮች አፍሪካዊ መፍትሔ የመፈለግ ጉዟችንን ለማፋጠን የአፍሪካ አገራት ወጣቶች አህጉራዊ አንድነትን ማጠናከር አለብን ሲሉ ተሳታፊዎች  አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡