የከፍተኛ ትምህርት ምርምር፣ ቴክኖሎጂ እና የኢንዱስትሪ ትስስር ኮንቬንሽን (HEART CONVENTION) አዘጋጅነት ለኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ተላለፈ

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ምርምር፣ ቴክኖሎጂ እና የኢንዱስትሪ ትስስር ኮንቬንሽን የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በየአመቱ እንዲያዘጋጅ የመግባቢያ ስምምነት ነሃሴ 26/2013 ዓም ተፈራረሙ፡፡

ስምምነቱን የተፈራረሙት በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዴኤታ ፕ/ር አፈወርቅ ካሱ እና የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዝዳንት ፕ/ር ጽጌ ገ/ማሪያም ናቸው።

በፊርማ ስነ ስርአቱ ላይም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በቀጣይ 10 አመት በአግባቡ ለመምራትና ለመስራት ከታቀዱ ግቦች መካከል ትምህርትና ስልጠና እና ሳይንስ ይገኝበታል፡፡ ዘርፉንም ዉጤታማ ለማድረግ 2021 የተዘጋጀዉ የከፍተኛ ትምህርት ምርምር፣ ቴክኖሎጂ እና የኢንዱስትሪ ትስስር ኮንቬንሽንና የሳይንስ ሽልማት አንዱ ነዉ ብለዋል፡፡

በመሆኑም ወደ “እዉቀት መር ኢኮኖሚ “ በሚል የተጀመረዉን ይህንን ትልቅ ስራ ለማስቀጠልና ለማሳካት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር አብረዉ መስራት ስለሚገባ ይህ ስምምነት ተደርጓል ብለዋል፡፡ በመሆኑም ለሚቀጥሉት ተከታታይ አመታት የሳይንስ አካዳሚዉ በባለቤትነትና በነጻነት እንዲመራዉ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ደግሞ እንዲያስተባብር ስራዉ ተሰጥቶታል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጽጌ ገ/ማርያም በበኩላቸው አካዳሚው እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለአንድ አላማ ተቀራርበዉ መስራት አለባቸዉ ያሉ ሲሆን የተሰጠዉን ሃላፊነት ለማሳካት እንደሚሰሩ ገልጸዉ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ይህንን እድል ሰለፈጠረ አመስግነዋል፡፡

ፕሮፌሰር ጽጌ ገ/ማርያም ምሁራንም መስፈርቱን የሚያሟሉ የአካዳሚዉ አባል በመሆን አብረዉን መስራት እንዲችሉ የማያሟሉም ለአባልነቱ የሚያበቁ አካዳሚያዊ ዉጤቶችን በማስመዝገብ እንዲሰሩ ጠይቀዋል ፡፡

የመጀመሪያው የከፍተኛ ትምህርት ምርምር፣ ቴክኖሎጂ እና የኢንዱስትሪ ትስስር ኮንቬንሽን (HEART CONVANTION 2021) “ወደ እውቀት-መር ኢኮኖሚ” በሚል መሪ ቃል ከሐምሌ 5 እስከ 8 /2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ መካሄዱ የሚታወስ ነዉ፡፡

ምንጭ ፦ (የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ፌስቡክ ገጽ)