የኢፌዲሪ ት/ት ሚኒስቴር እና የኢ.ሳ.አ. የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና፣ ሒሳብና ሥነጥበብ ትምህርትን በኢትዮጵያ በጋራ ለማሳደግ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራረሙ፡፡

የኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና፣ ሒሳብና ሥነጥበብ /STEAM/ ትምህርትን በኢትዮጵያ በጋራ ለማሳደግ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ /MoU/ ተፈራረሙ፡፡

የመግባቢያ ሰነዱን የኢፌዲሪ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ገረመው ሁሉቃ እና የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ የተፈራረሙት፣ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ፣ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ፅጌ ገብረማርያም እና በትምህርት ሚኒስቴር የሳይንስና ሒሳብ ትምህርት ማእከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብርሃም አለማየሁ በተገኙበት ነው፡፡፡

ሁለቱ ተቋማት የተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በምህንድስና፣ በሒሳብ እና በሥነጥበብትምህርቶች ዙሪያ የመምህራንን አቅም መገንባት፣ ቤተ ሙከራንና የሳይንስ መሳሪያዎችን የማደራጀትና ስታንዳርድ ዝግጅት፣ ተማሪዎችን በፈጠራ ሥራ ዙሪያ ማበረታታት፣ በሳይንስ ትምህርት የሴት ተማሪዎች ተሳትፎን ማሳደግ እንዲሁም የህፃናት የሳይንስ ትምህርት ማዕከልን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ማደራጀትና ወደ ሥራ ማስገባት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በጋራ ለመሥራት ያስችላቸዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትሩ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የሳይንስ እዉቀትና ባህልን በማስረጽ የህብረተሰቡ ህይወት እንዲሻሻል በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን  ገልፀው ስምምነቱ  በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና፣ የሒሳብ እና የሥነጥበብ ትምህርት ዘርፎችን የበለጠ ለማሻሻል እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሩ የአካዳሚውን የልጆች ሳይንስና የSTEM ማእከላትን ከጎበኙ በኋላ በሰጡት አስተያየት የልጆች የሳይንስ ማዕከል ህፃናት ሳይንስን እንዲወዱትና እየተዝናኑ እንዲማሩ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስላለው ልዩ ትኩረት ሰጥተን ወደ ተግባር መግባት ይኖርብናል ብለዋል፡፡ አያይዘውም ችግር ፈች የሆነው አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ የሙከራ ትግበራ ላይ በመሆኑ በቅንጅታዊ አሰራር አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር  ፅጌ ገብረማርያም በበኩላቸው አካዳሚው  ቀደም ሲል በሳይንስ፣ በሒሳብና በሌሎች የትምህርት ዘርፎችም በርካታ ሥራዎችን ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ሲሠራ መቆየቱን ገልጸው የሳይንስ አካዳሚው ከተቋቋመበት ጊዜ አንሥቶ በርካታ የምርምር ተግባራትንና በፖሊሲ ጉዳዮች መንግስትን የማማከር ሥራዎችን  እየሠራ ባለበት ወቅት ይህ ስምምነት መፈጸሙ በትምህርት ዘርፍ የምናከናውናቸውን ተግባራት የበለጠ ውጤታማ  ለማድረግ ያስችለናል ብለዋል፡፡ በሥነ ሥርዓቱ ማጠቃለያ የትምህርት ሚኒስትሩ እና ሚኒስትር ዴኤታዉ በሳይንስ አካዳሚዉ ቅጥር ግቢ ውስጥ የዛፍ ችግኞችን በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡