የኢትዮጵያ አካዳሚ ፕሬስ ያሳተመውን “ያልታሰበውየሕይወቴፈታኝጉዞእናየኢትዮጵያአብዮት ተሳትፎዬ’’የተሰኘመጽሐፍ አስመረቀ፡፡
በሌተና ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ እንግዳ ተጽፎ፣ በአካዳሚ ፕሬሱ የታተመው “ያልታሰበው የሕይወቴ ፈታኝ ጉዞ እና የኢትዮጵያ አብዮት ተሳትፎዬ” ግለታሪክ ትናንት ሐምሌ 15፣ 2013 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ጽ/ቤት ተመርቋል፡፡
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ በዕለቱ የተመረቀው የሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ “ያልታሰበው የሕይወቴ ፈታኝ ጉዞ እና የኢትዮጵያ አብዮት” የተባለው ግለታሪክ ፕሬሱ በከፍተኛ ደረጃ ጥራታቸውን አስጠብቆ ካሳተማቸው ስምንት መጻሕፍት መካከል አንዱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ መጽሐፉ ከሌሎቹ የአካዳሚው መጻሕፍት በተለየ፣ ለሕትመት ረጅም ጊዜ የወሰደ፣ በአንጻሩም የብዙ ባለሙያዎችን ተሳትፎ የጠየቀ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
መጽሐፉ ግለታሪክም ቢሆን “የአንድ ግለሰብ ሳይሆን የአገር ታሪክ የተዘገበበት መጽሐፍ ነው፣” ያሉት ዳይሬክተሩ፣ የኢትዮጵያ አካዳሚ ፕሬስ ይህንን በማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ እንዲሁም በዲፕሎማሲያዊ ታሪካችን ውስጥ የሚሞላቸው ክፍተቶች እንዳሉት፣ ከተመሳሳይ ግለታሪኮች በተሻለ ሁኔታ ከ1966 አብዮት ዋዜማ እስከ ደርግ ፍጻሜ ድረስ አገራችን ያለፈችባቸውን መንገዶች በስፋት እንደሚያሳይ ሊቃውንት እንደተመሰከረለትም አስታውሰዋል፡፡
ፕሮፌሰር ተከተል አያይዘዉ መፅሃፉ የኢትዮጵያን ታሪክ ከማሳየቱም ባሻገር ለተመራማሪዎችና አጥኚዎች በግብዓትነት የሚያገለግል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ የመጽሐፉን የሕትመት ታሪክ የተረኩ ሲሆን፣ ዶ/ር ያየህ ይራድ ቅጣው ደግሞ የመጽሐፉን ዳሰሳ አቅርበዋል፡፡
የመጽሐፉ ደራሲም የአደራረሳቸውን ታሪክ በአጭሩ ለታዳሚው ተናግረዋል፡፡ ከታዳሚዎች ቀርበው ለነበሩ ጥያቄዎችም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
መጽሐፉ በደርግ ዘመነ መንግሥት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነትና በተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሐላፊነት ቦታዎች ካገለገሉት ከሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ የሕይወት ተመክሮዎች እና ምልከታዎች አንጻር የአገራችንን ታሪክ ያስቃኛል፡፡
ደራሲዉ እዉነተኛ ታሪክን ለትዉልድ ለማስተላለፍ የተጉ መሆናቸዉን በምረቃዉ ሥነ ሥርአቱ ላይ የተገኙ ምሁራንና ደራሲያን ተናግረዋል ።
የአካዳሚዉ ፕሬስ ከ2,000 በላይ ገጾች የነበሩትን የዚህን መጽሐፍ ረቂቅ ለንባብ እንዲመች አድርጎ በማሳጠር በ700 ገጽ ያሳተመው ሲሆን፣ መጽሐፉን በዚህ መልኩ ለማዘጋጀት በተለየ ሁኔታ በርካታ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡
የምርቃት መርሃ ግብሩ ሂደት በፎቶ
ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ዋና ሥራ አስፈፃሚ
ፕ/ር ሽብሩ ተድላ
ኢ.ሳ.አ. መስራች አባል
የመጽሐፉ ምርቃት ስነ-ስርዓት
የመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች በከፊል
ሌ/ኮ/ል ብርሃኑ ባይህ
የመጽሐፉ ደራሲ
ቴዎድሮስ አጥላው
የኢትዪጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬስ – አርታዒ