የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ፣ በየወሩ ለሚያደርገው ህዝባዊ ገለፃና የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢንዱስትሪ ምህንድስና መምህር የሆኑትን ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣውን ጋብዞ፣ ጥራት ምንድን ነው? እንዴትስ ይተገበራል? በሚል ርእሰ ጉዳይ፣ ሐሙስ፣ ሰኔ 29፣ 2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ፋኩልቲ፣ የአካዳሚው አባላት፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችንና የሚዲያ ባለሞያዎች በተገኙበት አከናወነ፡፡
ገለፃውን ያደረጉት ፕሮፌሰር ዳንኤል እንዳብራሩት፣ ኢትዮጵያ ቀደምት የስልጣኔ ባለቤት ብትሆንም፣ እንደ መሪነቷ ልትቀጥል ያልቻለችውና፣ ከሃላ ተነስተው በሳይንስና ቴክኖሎጂ ከፍ ያለ ደረጃ የደረሱት አውሮፓውያን ሊቀድሟት የቻሉት የህዝቦቻቸው የልቦና ውቅር በጥራትና በምርታማነት ፍልስፍና የተቃኘና ለሳይንስ፣ ለቴክኖሎጂና ምርምር በሚሰጡት ትኩረት ላይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ፕሮፌሰር ዳንኤል በተጨማሪም ለተሳታፊዎች የጥራትን ጽንሰ-ሐሳብ በይበልጥ ግልፅ ያደረጉ ሲሆን “ጥራትን” በተሟላ መልኩ ለመተርጎም አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ ጥራት እንደ ተራ ቃል፣ በቀጥታ ቃል በቃል ተተርጉሞ የሚቀመጥ ሳይሆን የፍልስፍና አንድ አካል መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በአጭሩ ጥራት ማለት የደንበኛን ፍላጎት ማርካት፣ ከሚፈልገውም በላይ በላቀ ሁኔታ ማቅረብ ማለት ነው፡፡የአንድ አገልግሎት ጥራት የሚለካው በአገልግሎት ሰጪው አካል ፍላጎትና ይሁንታ ሳይሆን አገልግሎቱን በጠየቀው ደንበኛ ፍላጎት መሆኑን መረዳት እንዳለብን ገልፀዋል፡፡
እንደ ፕሮፌሰር ዳንኤል ገለፃ ሁለት የጥራት ምሶሶዎች ያሉ ሲሆን አንደኛው ሥራን በመጀመሪያ ጊዜም ሆነ ሁል ጊዜ በትክክል መሥራትና ሁለተኛው ደግሞ ሁልጊዜ የተሻለ የአሠራር መንገድ መከተል የሚባለው ነው፡፡ በመሆኑም ሁለቱ የጥራት ምሰሶዎች በትይዩ እና አቻ በአቻ መቆም ይኖርባቸዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር ምርታማነት ምን እንደሆነ እና በምርታማነት ዙርያ ያለውን ግራ መጋባት መጥራት እንዳለበት ጠቁመዋል ምርታማነት ከፍተኛ መጠን ያለው ምርት ማምረት አይደለም፡፡ ነገር ግን ምርታማነት ማለት ሥራው ላይ በሚውለው ልዩ ልዩ የግብአት እሴት እና ከዚያ በድርጅቱ ውሰጥ በግብአቱ ላይ እሴት ተጨምሮበት የሚገኘው ምርት ወይም አገልግሎት ሲወዳደር የሚያስገኘው ትርጉም ያለው ውጤት ማለት ነው፡፡
በተጨማሪም ጥራትንና ምርታማነትን ለመተግበር ከሚገፉን ምክንያቶች የመጀመሪያው፣ ደንበኛው የመጠየቁ ጉዳይ ነው፡፡ ደንበኛ ሁሌ የሚፈልገውን ይጠይቃል፣ በዚህም ደንበኛ ገበያውን ይመራዋል ማለት ነው፡፡ ወይም ደግሞ ደንበኛ ተኮር የሆነ ሥርዓት እንዲኖር ያደርጋል፡፡በተመሳሳይ መልኩ ፉክክርና ለውጥ ውጤታማነትና ምርታማነትን ለማምጣት አንድ አካል ሆነው መጓዝ አለባቸዉ፡፡
ፕሮፌሰር ዳንኤል ባቀረቡት ማጠቃልያ ላይ እንደተናገሩት ሁላችን አድጋና በልጽጋ ልናያት የምንናፋቃት ኢትዮጵያ አለችን፡፡ እውነት ነው በመፈክር ብዛትና በገደብ የለሽ ምኞት ብቻ ወደምንፈልግበት ግብ ልንደርስ አንችልም፡፡ የእያንዳንዳችን የልቡና ውቅር ለውጥ ግን በጥራትና የምርታማነት አስተሳሰብ ሲገነባና ይህንን ተረድተን መተግበር ስንጀምር እንደ ሀገር አድገንና በልጽገን፣ በየትኛውም ዓለም ብሔራዊ ክብራችን የተጠበቀ ይሆናል፡፡ የእየአንዳንዱም ግለሰብ የነፍስ ወከፍ ገቢ ሲያድግ የኑሮ ደረጃውም አብሮ ስለሚሻሻል፣ ህብረተሰባችን ጤናማና ደስተኛ በመሆን ኑሮን በማጣጣምና በአገሩ በመኩራት የበለጠ ሰርቶ አገሩን እንዲያሳድጋት ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል፡፡
በመጨረሻም ፕሮግራሙን ሲመሩ የነበሩት ጥሮፌሰር አበበ ድንቁ ለተመልካቹ የተነሱትን ፍሬ ሀሳብ ካስታወሱ በሀኋላ መድረኩን ለጥያቄ ክፍት አድርገው ፕሮፌሰር ዳንኤልም ለተመልካቾቹ ጥያቄዎች መልስ ሰጥተው ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡