የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የሴቶችን የዉሳኔ ሰጭነትና የአመራርነት ሚናቸዉን ከፍ ለማድረግ በሥርዓተ ጾታ እና ተዛማጅ ጉዳዮች ዙርያ ለአሰልጣኞች ስልጠና ሰጥቷል፡፡

አካዳሚዉ ከ International Network for Advancing Science and Policy (INASP) ከሚባል ግብረሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ከተለያዩ ድርጅቶችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለተውጣጡ ባለሙያ ሴቶች በሥርዓተ ጾታ እና ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ የአንድ ቀን የአሰልጣኞች የግንዛቤ ማሳደጊያ ስልጠና በድረገፅ እና በገፅ ለገፅ  ሰጥቷል፡፡

የአካዳሚዉ የፕሮግራም እና ግራንት ማናጀር አቶ አበበ መኩሪያው በሥልጠናው መክፈቻ መርሃ ግብር ላይ ለተሳታፊዎቹ እንደገለጹት አአካዳሚዉ ከ INASP ጋር በመቀናጀት የሥርዓተ ጾታን እኩልነትን በምርምር እና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲተገበሩ እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

 እንዲሁም  በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው የሚሰሩ ሴቶች በየዘርፉ ግንባር ቀደም ሚና መጫወት እንዲችሉ የተሻለ ግንዛቤ ለመፍጠር ታልሞ የተዘጋጀ ስልጠና መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አክለውም አካዳሚው የተለያዩ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት፣ በጥናት ላይ የተመሠረቱ አካታች ፖሊሲዎች እንዲወጡ የማማከር እንዲሁም ሴቶች መብቶቻቸው መከበሩን ማረጋገጥ  የሚችሉባቸውን የግንዛቤ የማሳደጊያ ሥራዎችን እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡

ሴቶች በሁሉም የሥራ መስኮች ችሎታቸውን በማሳደግ፣ ራሳቸውን በማብቃት፣ ተወዳዳሪና ግንባር ቀደም መሆን እንዳለባቸውና በዚህ ረገድ የማበረታቻ ሥርዓት ሊዘረጋ እንደሚገባ  ስልጠናውን የመሩት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የአካዳሚክስ አቅም ግንባታ ከፍተኛ አማካሪና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርት የሆኑት ዶክተር ሐረገወይን ፋንታሁን  አስረድተዋል፡፡

በአካዳሚው የሥርዓተ ጾታ ፎሬም አስተባባሪ ወ/ሮ ዮርዳኖስ ጌታሁን በበኩላቸው በዘርፉ ያሉ መልካም አጋጣሚዎችን እና ተግዳሮቶችን ለስልጠናው ተሳታፊዎች ያመላከቱ ሲሆን፤ የሴቶችን ንቁ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚቻለው በሥርዓተ ጾታ ዙሪያ  በጋራ የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥራዎችን በመሥራት እና በሕግ ማዕቀፎቹ ዙሪያ የሴቶችን ግንዛቤ በማስፋት በመሆኑ ይህ ስልጠና ቀጣይ ከጎንደር እና አሰላ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በቅንጅት ለሚካሄዱ ስልጠናዎች ጠቃሚ  ግብኣት ያገኘንበት ነው ብለዋል፡፡

ሴቶች ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን  ጠቅሰው የአመራርነትና የውሳኔ ሰጭነት ሚናቸውን በብቃት እንዲወጡ ግንዛቤያቸውን ማሳደግ እንደሚገባ በስልጠናው የተሳተፉ የኢትዮጵያ ሥርዓተ ጾታ ፎረም አባላት ሴቶች ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ እንደ ሀገር በሴቶች ላይ የተሻሉ እይታዎችና ግንዛቤዎች እየተፈጠሩ ያሉ ቢሆንም አሁንም ግን በጋራ መሠራት ያለባቸው ብዙ ተግባራት እንዳሉ ጠቅሰው የሴቶችን ፎረም ማጠናከር እንደሚገባም ተወስቷል፡፡

በአካዳሚው ውስጥ የሚገኙ ሴት ሠራተኞች በሚከናወኑ ማናቸውም ተግባራት እኩል ተሳታፊ እና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል በሥርዓተ  ጾታ ፎረም  አስተባባሪዋ አማካይነት  እየሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሥራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ በሥልጠናው መዝጊያ  ሥነ ሥርዓት  ላይ ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል፡፡