የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ከመንግሥት የተረከበውን እና በአዲስ አበባ በጉለሌ ክፍለ ከተማ የሚገኘውን ታሪካዊ ግቢ በዋና ጽሕፈት ቤትነት እየተገለገለበት ይገኛል፡፡ ይህ ታሪካዊ ግቢ እና ቤት በኢትዮጵያ ታሪክ በሀያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ስመጥር ጸሐፊ እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ መኖሪያ ቤት የነበረ ነው፡፡ አካዳሚው ይህንን ቤት ሕንፃው የቀድሞው ይዞታውን ሳይለቅ ውበቱ እና ለአገልግሎት ምቹነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ ለማደስ ሞክሯል፡፡ ይህ ሕንፃም የሥነ-ጥበብ ማዕከልን ለማቋቋም ዓይነተኛ ስፍራ መሆኑን አምኖ ሥራውን ጀምሯል፡፡
ስነ ጥበብ ማዕከሉ ሶስት አበይት ክንዋኔዎች ይካሄዱበታል፡፡ የመጀመሪያው አነስተኛ ሙዚየም ሲሆን፣ በሙዚየሙ ውስጥ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ መጻሕፍት፣ በልጃቸውና በልጅ ልጃቸው የተጻፉ መጻሕፍት፣ ስለመጻሕፎቻቸው የተጻፉና የተጠኑ ድርሳናት፣ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ከንጉሠነገሥቱ፣ ከሹማምንቱ ና ከቤተሰቦቻቸው የተነሱዋቸው ፎቶግራፎች እና እሳቸውና ዘመዶቻቸውን የሚገልፁ ቁሣቁሶች ይገኙበታል፡፡ ሁለተኛው የማዕከሉ አካል መጻሕፍት ቤት ሲሆን፣ በመጻሕፍት ቤቱ ውስጥ ስለ ኢትዮጵያ ቋንቋ ባህል ታሪክና ሥነጽሑፍ የሚያትቱ፣ በልዩ ልዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ቋንቋ የተሰናዱ፣ እንዲሁም የሳይንስ አካዳሚው አባላት የጻፍዋቸውንና የኢትዮጵያ አካዳሚ አሳታሚ ለንባብ ያበቁዋቸውን መጻሕፍት አካትቶ የያዘና ለየትኛውም አንባቢ ሕዝባዊ አገልግሎት የሚሰጥ ቤተመጻሕፍት ነው፡፡
ሶስተኛው የማዕከሉ አካል የሥነ-ጥበብ ባለሞያዎች፣ ፈጠራቸውን የሚያቀርቡበት፣ ዕውቀታቸውንና ክህሎታቸውን የሚያጋሩበት ቋሚ መድረክ ነው በመድረኩ፣ ሀገሪቱን የሚገልፁ፣ እሴቷን፣ ታሪኳን፣ ባህሏን ኪናዊ በሆነ መንገድ የሚያስተዋውቁ፤ በሥዕል፣ በፊልም፣ በቴአትር፣ በድርሰት፣ በቅርፃቅርጽ፣ በፎቶግራፍ፣ በዳንስና በሌሎች የጥበባት ዘርፎች ዝንባሌ ያላቸው ጀማሪና አንጋፋ ሙያተኞች ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት፣ ልምድ የሚለዋወጡበትና በአጫጭር ስልጠናዎች የሚሳተፉበት ይሆናል፡፡ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ማዕከሉ ዓመታዊ፣ መንፈቃዊ፣ ወርሃዊና ሳምንታዊ ፕሮግራሞችን ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የሥነ-ጥበብ ማዕከል፣ ከመጋቢት ወር 2009 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት መስጠት የጀመረ ማዕከል ነው፡፡