የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ለነባርና አዳዲስ ተመራማሪዎች የምርምር ሥራዎቻውን ለፖሊሲ ግብዓትነት ለማዋል የሚያስችላቸው የምርምር ተግባቦት ስልጠና አዘጋጀ፡፡
አካዳሚዉ በፖሊሲ እና በምርምር ውጤቶች መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላትና በመረጃ ላይ የተመሰረተ የፖሊሲ ዝግጅትና አፈጻጸምን ለማበረታታት ያለመ፣ ከነሐሴ 03 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ የምርምር ተግባቦት (Research Communication) ስልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡
ስልጠናው አካዳሚው ከዚህ ቀደም ያዘጋጀው ተመሳሳይ ስልጠና ቀጣይ ሲሆን በሥነ ሕዝብና ልማት ዘርፍ የሚገኙ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ የምርምር ሥራዎች ላይ የሚሳተፉ ከከፍተኛ ትምህርትና የምርምር ተቋማት ለተውጣጡ ነባርና ጀማሪ ተመራማሪዎች ስልታዊ (strategic) የምርምር ተግባቦት እውቀትና ክህሎት ለማዳበር ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡
የአካዳሚው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጽጌ ገብረማሪያም ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ፣ እየተተገበሩ የሚገኙ ፖሊሲዎች ብዙ ዓመታትን ማስቆጠራቸውንና በየጊዜው የሚወጡ ፖሊሲዎችም በጥናትና ምርምር ባለመታገዛቸው፣ ተፈጻሚነታቸውም ሆነ ውጤታማነታቸው ዝቅተኛ መሆኑን ገጸዋል፡፡
አካዳሚው የሳይንስ ዕውቀትንና ባሕልን የማሳደግና የማስፋፋት፤ እንዲሁም ለመንግሥትና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ሀገራዊ ጠቀሜታ ባላቸው ጉዳዮች ላይ በማስረጃ ላይ የተመሠረተ የፖሊሲ ምክር የመስጠት ዓበይት ዓላማዎችን ይዞ የተመሠረተ ተቋም እንደመሆኑ፤ በምርምር ውጤቶችና በፖሊሲ መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላት ስልጠናውን መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ስልጠናው ተመራማሪዎች ምርምሮችን ለፖሊሲ ግብዓትነት እንዲያውሉ የሚረዱ ሂደቶችን እንዲረዱ፣ ወሳኝ የፖሊሲ ተደራሲያንን ለመለየት እንዲችሉ፣ የምርምራቸው ውጤት በፖሊሲ ላይ ያለውን ተጽዕኖ ለመለየት እና የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅመው መልእክቶቻውን ማስተላለፍ የሚችሉበትን እውቀትና ክህሎት እንዲጨብጡ ለማድረግ ታስቦ እንደተዘጋጀ ፕሮፌሰር ጽጌ አስረድተዋል፡፡
በተመራማሪዎችና በፖሊሲ አውጪዎች መካከል መናበብ አለመኖሩን የገለጹት ፕሮፌሰር ጽጌ፣ በቀጣይ በፖሊሲ የሚመሩ ጉዳዮች ላይ በማተኮር አንጋፋና ወጣት ተመራማሪዎች ጥናቶችን እንዲያከናውኑና ፖሊሲዎች ሲዘጋጁም ሆነ ሲሻሻሉ ከምርምር ውጤቶች ጋር እንዲተሳሰሩ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥነ ሕዝብ ትምህርት ማዕከል መምህርና የፕላንና ልማት ኮሚሽን አማካሪ ዶክተር ተረፈ ደገፋ በበኩላቸዉ ሕዝብ የአንድ ሀገር ሀብትና የልማት ባለቤት ቢሆንም ከሀገሪቱ የመሰረተ ልማት፣ ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት አቅርቦትና ከአጠቃላይ እድገት ጋር ያልተጣጣመ የሕዝብ ቁጥር ብዛትና ያለው የሀብት ምጣኔ ባለመጣጣሙ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር እየተፈጠረ መሆኑን ባደረጉት ገለጻና ውይይት ወቅት አብራርተዋል፡፡
በመሆኑም፣ አካዳሚው ይህንን ሥልጠና ማዘጋጀቱ ተመራማሪዎች የምርምር ግኝቶቻቸውን ለፖሊሲ አውጭዎች ማስረዳት የሚችሉባቸውን እና ፖሊሲዎችም በምርምር ላይ የተመሠረቱ እንዲሆኑ አስተዋፅዖ ማበርከት የሚችሉባቸውን መንገዶች ለማሳየት እንደሚረዳም አስረድተዋል፡፡