የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ዋና መሥሪያ ቤት የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ሕንፃ በቅርስነት ተመዝግቦ የእውቅና የምስክር ወረቀት ተሰጠው። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባሕል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ለአካዳሚው የምስክር ወረቀት የሰጠው ስለቅርስ ጥናትና አጠባበቅ በወጣው አዋጅ ቁ. 209/92 አንቀጽ 17 ቁጥር 3 መሠረት ሕንጻው የቅርስነት እሴትን ያሟላ መሆኑን በማረጋገጥ ነው። በአዲስ አበባ፣ ጉለሌ ክፍለ ከተማ የሚገኝው የአካዳሚው ዋና መስሪያ ቤት እና አካዳሚው በሥነ ጥበባት ማዕከልነት እየተገለገለበት የሚገኘው ሕንጻ በኢትዮጵያ ታሪክ በሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ ስመጥር ደራሲ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የታሪክ ጸሐፊ፣የነበሩት ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ መኖሪያ የነበረ ሲሆን የሥነጥበባት ማዕከሉም በስማቸው የተሰየመው አበርክቷቸውን ለመዘከር ታስቦ ነው።