የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በኢትዮጵያ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን የልጆች የሳይንስ ማዕከል አስመረቀ::

የኢትዮጵያ  ሳይንስ  አካዳሚ  በኢትዮጵያ  በአይነቱ  የመጀመሪያ  ሆነውን  የልጆች  የሳይንስ  ማዕከል  አስመርቋል፡፡

አካዳሚዉ ከጀርመን  የባህል ተቋም  እና  ጀርመን  ሀገር  ከሚገኘው  ፌኖሜንታ ሳይንስ ማዕከል ጋር በመተባበር ማቋቋሙም ተገልጿል፡፡

በማእከሉ ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተዉ  ንግግር  ያደረጉት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ  ሚኒስቴር  ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ የኢትዮጵያ መንግስት ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ልማት በሰጠው ልዩ ትኩረት በርካታ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉን አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ  ሳይንስ  አካዳሚ ይህንኑ በማጠናከር የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑትን ሕፃናት በሳይንስና ቴክኖሎጂ እውቀት ተኮትኩተው እንዲያድጉና ለሀገራቸዉ ሁሉ አቀፍ ልማትና ብልጽግና ጉልህ ሚና እንዲጫወቱ በሀገራችን በአይነቱ  የመጀመሪያ  የሆነውን  የልጆች  የሳይንስ  ማዕከል ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ማቁቋሙ የሚበረታታ ድርጊት መሆኑን ገልጸዋል፡፡  

የሳይንስ አካዳሚዉ ፕሬዚደንት ፕሮፌሰር ፅጌ ገብረማርያም ባደርጉት ንግግር አካዳሚው  የሳይንስ ዕውቀትንና ባሕልን ለማሳደግ እንዲሁም ህጻናት  በተመቻቹ የቴክኖሎጂ ቁሳቁሶች እየተዝናኑ ስለሳይንስና ቴክኖሎጂ ፅንሰ-ሐሳብና አሠራር ዕውቀት እንዲያገኙና ለዘርፉ ያላቸው ዝንባሌ እንዲያድግ ታቅዶ  መቋቋሙን አብራርተዋል፡፡

አካዳሚዉ በዋናነት የሳይንስ ዕውቀትንና ባሕልን የማሳደግና የማስፋፋት፤ እንዲሁም ለመንግስትና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት በማስረጃ ላይ የተመሰረተ የፖሊሲ ምክር የመስጠት ዓበይት ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸዉን ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

የማዕከሉ ግንባታ ከተጀመረ በ3 ዓመት የተጠናቀቀ ሲሆን ለግንባታዉ የጀርመን ባህል ማዕከል 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር፣ የኢትዮጵያ የሳይንስ አካዳሚ መንግስት የሳይንስ ዘርፍን ለማጠናከር ከስጠዉ 40 ሚሊዮን ብር  7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር እና የጀርመኑ የሳይንስ ማዕከል ፌኖሜንታ 7 ሚሊዮን ብር ወጪ ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱን ገልጸዋል።

ፕሮፌሰር ፅጌ አያይዘዉ አገራችን ወቅቱ በሚፈልገው የእድገት አቅጣጫና ፍጥነት እንድትጓዝ ለማድረግ የሳይንስ እውቀት ማበልፀጊያ ተቋማት ግንባታ የሳይንስ ማህበረሰብ ምስረታና የአገር በቀል እውቀት አጣምሮ መስራት እንዳለበት ገልጸዉ ለዚህ አላማ ስኬት የኢትዮጵያ መንግስት፣ የጀርመን  የባህል ተቋም  እና  ጀርመን  ሀገር  የሚገኘው  ፌኖሜንታ ሳይንስ ማዕከል ላደረጉት ቴክኒካዊና ፋይናንስ ድጋፍ ምስጋናቸዉን አቅርበዋል፡፡

የጀርመን  የባህል ተቋም  እና  ጀርመን  ሀገር  የሚገኘው  ፌኖሜንታ ሳይንስ ማዕከልን ወክለዉ በምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉ ተወካዮቻቸዉ በተለያየ የእድሜ ደረጃና የትምህርት እርከን ላይ የሚገኙ የማኀረሰቡን አካላት ግንዛቤ ለማሳደግና የሳይንስ እውቀትን ለማስረፅ  ማእከሉ ጉልህ ሚና እንደሚኖረዉ ገልጸዋል፡፡

የሳይንስ  አካዳሚዉ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ ባስተላለፉት መልእክት የበርካታ አገር በቀል እውቀቶች፣ የጥንታዊ ታሪክ ቅርሶችና የተፈጥሮ ጸጋ ባለቤቶች በመሆናችን እነዚህን በሳይንሳዊ መንገዶች በማዘመን ለህብረተሰባችን ህይወት መሻሻል የጀመርናቸዉን ዉጥን ተግባራት ከግብ ለማድረስ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ብርቱ ርብርብ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡

የልጆች  የሳይንስ  ማዕከል የምረቃ ሥነ-ስርዓት

ፕሮፌሰር ፅጌ ገብረማርያም

የኢትዮጵያ  ሳይንስ  አካዳሚ ፕሬዚደንት

ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ

የኢትዮጵያ  ሳይንስ  አካዳሚ ዋና ሥራ አስፈፃሚ

ዶ/ር እንግዳወርቅ አሰፋ

የኢትዮጵያ  ሳይንስ  አካዳሚ ም/ሥራ አስፈፃሚ

ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ  ሚኒስቴር  ሚኒስትር ዴኤታ

አቶ ወንድወሰን በለጠ

የሳይንስ ማዕከሉ ዳይሬክተር

የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ምረቃውን በተመለከተ የሰጡትን ሽፋን ከዚህ በታች የሚገኙትን ማስፈንጠሪያዎች በመጫን ይከታተሉ፡፡

Balageru TV

EBS TV