የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በአካዳሚው ፕሬስ ያሳተመው የትውልድ አደራ የተሰኘ መጽሐፍ ተመረቀ

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በአካዳሚው ፕሬስ አማካኝነት ያሳተመውን የልዑል ራስ መንገሻ ሥዩምን የትውልድ አደራ የተሰኘ ግለ-ታሪክ መጽሐፍ መጋቢት 7/2010 ዓ.ም በዋናው ጽ/ቤት በይፋ አስመረቀ፡፡

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በአካዳሚው ፕሬስ አማካኝነት ያሳተመውን የልዑል ራስ መንገሻ ሥዩምን የትውልድ አደራ የተሰኘ ግለ-ታሪክ መጽሐፍ መጋቢት 7/2010 ዓ.ም በዋናው ጽ/ቤት በይፋ አስመረቀ፡፡

የአካዳሚው ፕሬስ የአርታኢያን ቦርድ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር አለማየሁ ተፈራ የምረቃ ሥነ-ስርዓቱን በንግግር የከፈቱ ሲሆን፤  ፕሮፌሰር አለማየሁ “የኢትጶጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሳይንሳዊ ባህልና ፈጠራ እንዲጎለብት ከመስራትም ባሻገር የህብረተሰቡ ዕውቀት እንዲሻሻል በተፈጥሮና ማህበራዊ ሳይንስ፣ በስነ-ሰብ፣ በታሪክ እና በስነ-ጥበባት ዙሪያ በልዩ ልዩ ፀሐፍትና ተመራማሪዎች የተዘጋጁ ጽሑፎችን እየተቀበለ በባለሙያ እያስገመገመና እያተመ ለማህበረሰቡ የሚያቀርብበትን የራሱን ፕሬስ አቋቁሞ እየሠራ ይገኛል” በማለት ፕሬሱ የተቋቋመበትን ዓላማ ገልጸዋል፡፡

ይህ የትውልድ አደራ በሚል ርዕስ ለምርቃት የበቃው መጽሐፍ፣ በልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም የተዘጋጀ የሕይወት ታሪካቸው ሲሆን፤ ባለታሪኩ የተለያዩ ጠቅላይ ግዛቶች አስተዳደርና የሥራና መገናኛ ሚኒስቴር ሚንስትር ሆነው ያገለገሉ ናቸው፡፡ መጽሐፉ በእነዚህ ኃላፊነቶቻቸው ወቅት ከሠሯቸው ሥራዎች በተጨማሪ ከልጅነታቸው እስከ አሁን ድረስ ያለፉበትን የልጅነት ዕድገት፣ የቤተሰብ ታሪክ፣ የፖለቲካ ውጣ ውረድና ማኅበራዊ ሕይወትን የሚዳስስ ከመሆኑ ባሻገር፤ ከአብዮቱ ጋር በተያያዘ ልዑል ራስ በትጥቅ ትግል ያሳለፉበትን ዘመን የሚያካትት ዝርዝር ሲሆን፤ የታሪክ ኤሜሪተስ ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ በመጽሐፉ የጀርባ ሽፋን ላይ በሰጡት አስተያየት ለዘመኑ ታሪክ እንደቀዳማይ ምንጭ የሚቆጠር ነው በማለት ለተጨማሪ የታሪክ ምርምር አጋዥ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የታሪክ ኤሜሪተስ ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀም ስለመጽሐፉ ይዘትና ስለ ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም የቀደመ ታሪክ የሚያብራራ ሙያዊ ጽሁፍ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል፡፡ የመጽሐፍ ምረቃው የልዑል ራስ ቤተሰቦች፣ ወዳጆች፣ ተጋባዥ እንግዶች እና የሚዲያ አካላት በተገኙበት በድምቀት ተከውኗል፡፡

Prof GebruParticipants

ልዑል ራስም መጽሐፉ አንዲታተም ላደረገው ለኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ፤ ለኅትመት በሚሆን መልኩ በማዘጋጀትና እስከመጨረሻው ድረስ ለንባብ እንዲበቃ ላደረጉት ለፕሬሱ አርታኢ ለአቶ ብርሃኑ ደቦጭ እና እገዛ ላደረጉ ተቋማትና ግለሰቦች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

Photo with Professor MasreshaLeul ras

በሚቀጥሉት ጥቂት ወራትም፣ ‹‹የህያው ምሥጢር›› በሚል ርዕስ በፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ የተዘጋጀውና በመሠረታዊ ሳይንስ ግንዛቤ ዙሪያ የሚያጠነጥን መጽሐፍ ለኅትመት ይበቃል፡፡ እንደዚሁ ግምገማው የተጠናቀቀለት በአቶ ሰይፉ መታፈሪያ የተዘጋጀውና በምሥራቅ ሐረርጌ አካባቢ ያሉ የኦሮሞ ሕዝብ ነዋሪዎች የሥራ ላይ ግጥሞቻቸው ዙሪያ የተሠራ የፎክሎር ምርምራዊ ጽሑፍ በአካዳሚው ፕሬስ ለኅትመት እየተዘጋጀ ይገኛል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *