የኢትዮጵያ ሙዚቃ ለማህበረሰብ መሻሻል እየዋለ አይደለም

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ 33ኛውን እና የዓመቱን የመጨረሻውን የሳይንሳዊ ገለፃና ውይይት መርሐ-ግብር ሙዚቃና ማህበራዊ ፋይዳው በተሰኘ ርዕሰ-ጉዳይ ላይ አካሄደ፡፡

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ 33ኛውን እና የዓመቱን የመጨረሻውን የሳይንሳዊ ገለፃና ውይይት መርሐ-ግብር ሙዚቃና ማህበራዊ ፋይዳው በተሰኘ ርዕሰ-ጉዳይ ላይ አካሄደ፡፡

ገለፃውን አርቲስት አብርሃም ወልዴ ያቀረበ ሲሆን በኢትዮጵያ የሙዚቃ እድገትና በህብረተሰቡ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ትርክት ውስጥ ያለውን ፋይዳ መነሻ በማድረግ ውይይቱ ተካሂዷል፡፡ አርቲስት አብርሃም በገለፃው የኢትዮጵያ ሙዚቃ በህብረተሰቡ ውስጥ ያለን ባህል፣ አስተሳሰብ፣ እና መልካም መስተጋብር መርምሮ ከማሳየት ይልቅ ወደሌላው ዓለም የፈጠራ ሥራዎች የመቀላወጥ ችግር ይስተዋልበታል ብሏል፡፡ ከቀድሞዎቹ ውስጥ በጣም ጥቂት ቢሆኑም ደፍረው ለህብረተሰብ ለውጥ የደከሙ፣ የተበላሸ የማህበራዊና የፖለቲካ ሥርዓት የሚተቹ ነበሩ ያለው አርቲስት አብርሃም፤ ዛሬም ድረስ ጠንካራ ሙዚቀኞች አሉ ብሏል፡፡ ነገር ግን አብዛኛው በዘርፉ የተሰማራው የሙዚቃ አሳታሚም ሆነ ባለሙያ የሙዚቃን ማህበራዊ ፋይዳ በመዘንጋት ሐብት መፍጠሪያ መንገድ አድረጎታልም ብሏል፡፡ ለዚህም የኢኮኖሚ እና የአመለካከት ድህነት የመጀመሪያው ምክንያት እንደሆነ አቅራቢው ተናግሯል፡፡

ተሳታፊዎች

የፖለቲካ ጥገኝነት ሌላው ዋነኛ የችግሩ ምንጭ እንደሆነም ተነስቷል፡፡ የኢትዮጵያ ሙዚቃ የሚታወቀው ላለው ሥርዓት ማጎብደድ እንጂ፣ የየዘመኑን አፋኝ የፖለቲካ ሥርዓቶች ፍላጎትና ጫና ተቋቁሞ ለዕውነተኛ የህብረተሰብ ለውጥ እየዋለ አይደለም ያሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ኤሜረተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር ባህሩ አክለውም በርግጥ ትላንት ጫናውን አሸንፈው በሙዚቃዎቻቸው ትግል ያደረጉ፣ ዛሬም አድርባይነትን አሻፈረኝ ያሉ ጠንካራ ወጣት የሙዚቃ ባለሙያዎች እንዳሉ ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሙዚቃ ኢንዱስትሪ እንዳያድግ እና የህብረተሰብን ንቃተ-ሕሊና ለማነፅ እንዳይውል ካደረጉት ሌሎች ችግሮች ውስጥ የፈጠራ ነጻነት እጦት እና የምርምር ችግር እንደሆም ተሳታፊዎች በስፋት አንስተዋል፡፡ ፈጠራ ነጻነትን ይፈልጋልም ተብሏል፡፡ ከፖለቲካዊ ሃይልና ጫና ቀንበር ወጥቶ ሙያዊ ደረጃ እንዲይዝና ለማህበረሰቡ የሥነ-ልቦና፣ የሥነ-ምግባርና የነፃነት አጋር እንዲሆን ከተፈለገ ጫናውን ማስወገድ እንደሚያስፈልግ ተሳታፊዎች በተደጋጋሚ አውስተዋል፡፡

ተሳታፊዎች

ከሙያተኛው ጥረት በዘለለ ሊታይና ማስተካከያ ሊደረግበት የሚገባው ”የሙዚቃ ምርምርና ጥናት ደካማነት ነው በማለት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጡ ተሳታፊ ሌላውንል የችግሩን ገጽታ አንስተዋል፡፡ ዘርፉን ለማሳደግ ሳይንሳዊ ትምህርት መሰጠት ከጀመረ ግማሽ ክፍለ-ዘመን የሚሆነው ቢሆንም፣ ለሙዚቃው እድገት የዋለው ውለታ ግን በቂ እንዳልሆነ በውይይቱ ተነስቷል፡፡

ተሳታፊዎች

በመሆኑም ዘርፉ እራሱን መመርመር፣ ማሳደግ፣ መምራት እንዲችል እና ፈጠራን አጎልብቶ ለህብረተሰብ አኗኗር፣ አመለካትና ስብዕና መዳበር ድርሻውን እንዲወጣ ከተሳታፊዎች ጥሪ ቀርቧል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *