በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ አዘጋጅነት በየወሩ የሚካሄደው የሳይንሳዊ ገለፃና ውይይት መድረክ ታኅሳስ 26 ቀን 2010 ዓ.ም “የቡና ተክል ዕድገትና ምርት ከአየር ንብረት ለውጥ አንፃር” በሚል ርዕስ ተካሄደ፡፡ በመርሐ-ግብሩ በኢትዮጵያ ያለው የቡና ልማት ሥራ፣ የቡና ሥነ-ምሕዳርና የአመራረት መስተጋብር እንዲሁም በቀጣዩ አሥር ዓመት የቡና ተክል ዕድገትና
በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ አዘጋጅነት በየወሩ የሚካሄደው የሳይንሳዊ ገለፃና ውይይት መድረክ ታኅሳስ 26 ቀን 2010 ዓ.ም “የቡና ተክል ዕድገትና ምርት ከአየር ንብረት ለውጥ አንፃር“ በሚል ርዕስ ተካሄደ፡፡ በመርሐ-ግብሩ በኢትዮጵያ ያለው የቡና ልማት ሥራ፣ የቡና ሥነ-ምሕዳርና የአመራረት መስተጋብር እንዲሁም በቀጣዩ አሥር ዓመት የቡና ተክል ዕድገትና ምርት ከአየር ንብረት ለውጥ አንፃር ላይ ያተኮሩ ሳይንሳዊ ገለጻዎች በምሁራን እና በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማት የሥራ ኃላፊ ቀርቦ ጥልቅ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በኢትዮጵያ ቡና በሦስት ዋና ዋና መንገዶች ይመረታል ያሉት የመጀመሪያው አቅራቢ ዶ/ር ታደሠ ወ/ማርያም፤ በተፈጥሮ ደን ውስጥ፣ በትንንሽ የአ/አደር ይዞታና በሰፋፊ የቡና እርሻ ዋነኞቹ ተጠቃሽ ዘዴዎች አንደሆኑ አውስተዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ታደሠ ገለጻ እ.ኤ.አ ከ1970 እስከ 2000 ባለው ጊዜ ብቻ የደቡብ ምዕራብ ከፍተኛ አካባቢዎች እስከ 60 በመቶ የሚሆነው የደን ሽፋን የመመንመን አደጋ ገጥሞታል፡፡ “ይህ የአገሪቱ አካባቢ ከፍተኛ ቡና አብቃይ ቢሆንም፤ በአማካይ በዓመት 1 በመቶ የሚሆን የደን ሽፋን እየወደመ የተፈጥሮ ቡና ደን ከፍተኛ መሳሳት እየተስተዋለበት ምርቱም እየተዳከመ መጥቷል“ በማለት ችግሩን አሳይተዋል፡፡
አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማት ባለስልጣን የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ኤክስቴንሽን ዳይሬክተር በበኩላቸው አገር አቀፍና ክልላዊ የቡና ልማት ሥራዎች ገፅታና ፈተናዎችን በማስመልከት የመንግስት አቅጣጫዎችንና የታቀዱ ተግባራትን ለታዳሚው አቅርበዋል፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም ታዋቂና ልዩ ጣዕም ያላቸው የቡና አይነቶችን በይርጋ ጨፌ፣ ሲዳማ፣ ሐረር፣ ጅማ፣ ነቀምቴ፣ ሊሙ፣ ቴፒ፣ በበቃ እና በሌሎች አካባቢዎች በዓመት በአማካይ ከ500 ሺህ እስከ 700 ሺህ ቶን ቡና ታመርታለች ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ከ25 በመቶ በላይ የህብረተሰብ ክፍል መተዳደሪያ የገቢ ምንጭ በመሆን ሰፊ የዓለም ገበያ ድርሻም እንደያዘ በስፋት ተናግረዋል፡፡ የሆነ ሆኖ ግን የምርቱ መጠንና ጥራቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ እንደሆነ አቶ ብርሃኑ ገልፀዋል፡፡ ለምርቱ ማነስ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም ዓብይ መንስዔዎቹ የአየር ንብረት ለውጥ ማለትም የዝናብ እጥረት፣ የሙቀት መጨመር እና ያልተለመዱ የበሽታና የተባይ አይነቶች መከሰት፣ ከግንዛቤ እጥረት የመነጨ የደን ውድመትና የአፈር መሸርሸር እንዲሁም ምርትን ለማሻሻል ሳይንሳዊ መንገዶችን ያለመከተል እንደሆኑ አፅንዖት ሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻም በፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው “የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ በቀጣዮቹ ዐሥርት ዓመታትና የመቋቋሚያ መንገዶቹ“ የተሰኘ ሳይንሳዊ ገለጻ ቀርቧል፡፡ ፕሮፌሰር ሰብስቤ በዋናነት የአየር ንብረት ለውጥ ያለበት ሁኔታ፣ ወደፊት ሊፈጥር ስለሚችለው ጫናና መፍትሔዎች በዝርዝር ዳስሰዋል፡፡ እንደ አቅራቢው ገለፃ የኢትዮጵያ አማካይ ዓመታዊ የሙቀት መጠን በ2060ዎቹ አሁን ካለበት 1.1 ወደ 3.1 ዲግሪ ሴሊሸስ የሚጨምር ሲሆን፤ እንደሚኖረው የካርቦን ልቀት መጠንና ሁኔታ በ2090ዎቹ ወደ 5.1 ዲግሪ ሴሊሸስ የሙቀት መጠን ድረስ ሊንር እንደሚችል ይተነበያል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ ሞዴል ትንበያ መረጃዎች አገራችን በአራቱም ወቅቶች ሙቀት እየተስተዋለባት መሆኑን ያሳያል፤ ይህ የሙቀት መጨመር የዝናብና የዕርጥበት ወቅቶችና ሁኔታዎች መዘበራረቅ ከማስከተልም አልፎ ከ15 ሚሊዮን በላይ ቡና አምራች አርሶ አደሮችን ሕልውና ይገዳደራል ብለዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ የአየር ንብረት ሁኔታን የመከታተያ ሥርዓት መፍጠር፣ የአየር ንብረት ለውጥ በቡና ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ጫና መለየትና አፋጣኝ ዕርምጃ መውሰድ፣ በተቀናጀ ሁኔታ በከፍተኛ አካባቢዎች አዳዲስ የቡና አብቃይ ስነ-ምሕዳሮችን ማበልፀግ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡
ምሁራኑ ከተሳታፊዎች የቡና ኢኮኖሚ ዘለቄታዊነትና አማራጭ የኢኮኖሚ ዘርፎችን አስመልክቶ ለተጠየቁ ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል፡፡ በመረጃ ላይ የተመረኮዘ ሳይንሳዊ መፍትሔና የፖሊሲ አቅጣጫ ካልተነደፈ በቅርቡ የቡና ዕድገትና ምርት በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ቀጥተኛ ተጎጂ ሊሆን እንደሚችል ሦስቱም አቅራቢዎች ይስማማሉ፡፡ በዚህ በዋናነት የግብርናው ዘርፍ ብሎም የቡና ምርቱ ቀጥተኛ ተጠቂ ይሆናል፡፡ እዚህ ደረጃ ከመደረሱ አስቀድሞ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የቡና ልማት አቅጣጫ መከተል አማራጭ እንደማይኖረው በጉባኤው ድምዳሜ ላይ ተደርሷል፡፡
ውይይቱን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ሕይወት ትምህርት ክፍል ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ዘሪሁን ወልዱ መርተውታል፡፡