የአውራምባ ማኅበረሰብ ታሪክ እና እሴቶች መሰነድ እንዳለባቸው ተገለጸ፡፡

የአውራምባ ማኅበረሰብ አባላት ታሪካቸው እና እሴቶቻቸው በሚሰነዱበት ሁኔታ  ላይ ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ጋር በአካዳሚው ቅጥር ግቢ ውስጥ ውይይት አካሂደዋል፡፡

አዲስ አበባ፡ ጥቅምት 19/2014: የውይይቱ ዓላማ የአውራምባ ማኅበረሰብን አምሳኛ የምሥረታ ዓመት ምክንያት በማድረግ፣ ለምርምር የሚጋብዙትን እና መልካም ተመክሮ የሚቀሰምባቸውን የማኅበረሰቡን መልካም አስተሳሰብ፣ ፍልስፍና፣ በጎ ምግባር እንዲሁም ጠንካራ የሥራ፣ የመተሳሰብና የመረዳዳት ባህል ለአገራችንና ለዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ክፍል ለማሳወቅ የሚቻልበትን መንገድ ለማመቻቸት ነው፡፡

በውይይቱ የሳይንስ አካዳሚው የሥራ ሓላፊዎችና የአውራምባ ማኅበረሰብ መሥራቹን ዙምራ ኑሩን ጨምሮ የማኅበረሰቡ አባላት እና ወዳጆች የተሳተፉ ሲሆን፤ አካዳሚው አገር በቀል እውቀቶችን የማስቀጠልና የማበረታታት ሥራዎችን የሚሠራ አገር አቀፋዊ ድርጅት መሆኑን የጠቆሙት የአካዳሚው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ፣  የጥራት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የማሕበረሰቡን እሴቶች እና ታሪክ ለመሰነድ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ የበኩሉን እገዛ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆኑን  ገልጸዋል፡፡

የአውራምባ ማኅበረሰብ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በደቡብ ጐንደር ዞን አስተዳደር በፎገራ ወረዳ  የሚገኝ ሲሆን በፍጹም እኩልነት የሚያምን፣ የሰላምና የፍቅር ተምሳሌት፣ በጠንካራ የሥራ ባህሉና በመልካም ሥነ ምግባሩ ታዋቂነትንና ዝናን እያተረፈ የመጣ ማኅበረ ሰብ እንደሆነ የማኅበረሰቡ መሥራች ዙምራ ኑሩ አብራርተዋል፡፡

የማኅበረሰቡ መሪዎች እና የአምሳኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን በማስተባበር ላይ የሚገኙ በጎ ፈቃደኞችም አካዳሚው በመጽሐፍ፣ በዘጋቢ ፊልም ዝግጅት እና በአውደ ጥናቶች የአውራምባን እሴቶች ለትውልዶች ለማስተላለፍ በሚደረገው ሥራ ላይ ለመሳተፍ በመስማማቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል፡፡ በጋራ መሥራት የሚቻልባቸውን ጉዳዮች ለመለየት የመነሻ ሰነድ ለማዘጋጀትም ቃል ገብተዋል፡፡

እንግዶቹ የአካዳሚው የሳይንስ ማዕከል እና ሌሎችም በቅጥር ግቢው የሚገኙ መስህቦችን ጎብኝተዋል፡፡

ማህበረሰቡ በፍትሐዊነቱ፣ በጠንካራ የመልካም አስተዳደርና ባሕሪዉና የሌሎች የመልካም እሴቶች ባለቤት በመሆኑ የስራ ባህል ባለቤት  በመሆናቸው  የበርካታ  ጎብኚዎችን ቀልብ በቀላሉ መሳብ የቻለ ማኅበረሰብ ለመሆንም መብቃቱን ስለማኅበረሰቡ እሴቶች የተካሄዱ ጥናቶች ይገልጻሉ፡፡