የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ጥራት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለጸ

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ጥራት ችግር እና የሥራ አጥነት ትሥሥር ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት ሚያዝያ 25/2010 ዓ.ም አካሄደ፡፡

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ጥራት ችግር እና የሥራ አጥነት ትሥሥር ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት ሚያዝያ 25/2010 ዓ.ም አካሄደ፡፡ በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሄደው ገለፃ በዘርፉ ጥናት ባደረጉ ምሁራን እና በፌደራል የቴክኒክና ሙያ ኤጀንሲ የሥራ ኃላፊዎች የውይይት መነሻ ጽሁፍ ቀርቦ በባለድርሻ አካላት ምክክር ተደርጎበታል፡፡

Public

በኢትዮጵያ ዕድሜው ለሥራ የደረሰ (ከ15-64 ዓመት የሆነው) አምራች የህብረተሰብ ክፍል እ.ኤ.አ በ2015 ላይ 55 በመቶ ከነበረበት በክፍለ-ዘመኑ መገባደጃ ላይ  ወደ 63.3 በመቶ በማደግ ሰፊ አምራች ኃይል የሚፈጠር ሲሆን፤ በአንፃሩ በመጠነ-ውልደትና ሞት ማሽቆልቆል ሳቢያ፣ ለኤኮኖሚው አስተዋፅዖ የሌለው (economically dependent) ዕድሜው ከ0-14 የሚሆነው ቁጥሩ 41.5 በመቶ ከነበረበት ወደ 16.8 በመቶ ዝቅ እንደሚል ይተነበያል፡፡ በዚህ የሥነ-ሕዝብ አወቃቀር ሽግግር ሂደት (demographic transition) በርካታ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች እየተፈጠሩ ይሄዳሉ፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ ዶ/ር ሰዒድ ኑሩ በዕለቱ ኢትዮጵያ ውስጥ እየመጣ ያለውን የሥነ-ሕዝብ አወቃቀር ሽግግር ጠቀሜታ ከትምህርት ጥራትና ሥራ አጥነት ጋር በማዛመድ አጭር ጥናት አቅርበዋል፡፡ አቅራቢው የሕዝብ ብዛት በመጨመሩ በገጠር ውስን ቢሆንም ድብቅ ሥራ አጥነት (disguised unemployment) ማለትም በ1953 ዓ.ም 1.2 ሄክታር መሬት የአንድ አርሶ አደር ይዞታ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ያንኑ ተመሳሳይ የመሬት መጠን የአምስት ሰዎች ይዞታ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል፡፡ ይህ ማለት አራቱ ሰዎች ድብቅ የሆነ ወይም ያልተመዘገበ ሥራ አጥነት ውስጥ ይገኛሉ፤ በከተማም ከፍተኛ የሆነ ሥራ አጥነት እንደሚስተዋልም ገልጸዋል፡፡

ይህን ችግር ለመቅረፍና ወጣቱን ወደ ሥራ ለማስገባት በአገር አቀፍ ደረጃ የተዘረጋው የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተደራሽነት አበረታች ቢሆንም የጥራት ሁኔታ አሁንም ትልቁ ችግር እንደሆነ ቀጥሏል ይላሉ አቅራቢው፡፡ ዶ/ር ሰዒድ እያደገ የሚመጣ የሕዝብ ቁጥር ጥራት ባለው ትምህርት ታግዞ ለኤኮኖሚው ግብዓት ካልሆነ የሕዝብ ቁጥር መጨመር ትሩፋት መሆኑ ቀርቶ ሸክም ወደመሆን ይሸጋገራል በማለት ተዛምዶውን እና አስከፊ ውጤቱን አብራርተዋል፡፡ ይሁን እንጂ፣ በፌደራል የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኤጀንሲ የደረጃ ምደባና ምዘና ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ንግስት መላኩ፣ ጥራትን ለማስጠበቅ የገበያውን ፍላጎት መሠረት ያደረገ የሥርዓተ-ትምህርት ቀረፃ በማድረግ፣ ብቁ አሠልጣኝ በመመደብ፣ መመዘኛ ደረጃ በማዘጋጀት እና ሙያውን ከኢንዱስትሪ ጋር በማስተሳሰር እአተሠራ ነው ይላሉ፡፡ በፌደራል የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኢንስቲትዩት የአካዳሚክ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ተሻለ በሬቻም በዝግጅት ምዕራፍ ያሉት ተግባራት የተሻለና አበረታች መሆኑ ላይ በወ/ሮ ንግስት ሀሳብ የሚስማሙ ቢሆንም፣ አተገባበር ላይ ክፍተቶች በመኖራቸው ሥልጠናዎቹ ከጥራት ችግር እንዳይላቀቁ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ ተሻለ ምልከታ፤ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠናዎች ብቁ ባልሆኑ አሠልጣኞች እየተሰጡ መሆኑ፣ ከኢንዱስትሪ ጋር በማስተሳሰር ሠልጣኞች በሥርዓተ-ትምህርቱ መሠረት 70 በመቶ የሚሆነውን የትምህርት ጊዜ ሙሉ በሙሉ በኢንዱስትሪዎች ውስጥ እንዲማሩ ባለመደረጉ እና የሥልጠና መስኮች አይነትና ብዛት ከገበያው ጋር የተጣጣመ ባለመሆኑ ጥራቱን ማሻሻል እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡

ሌላው የፓናል አቅራቢ የሆኑት ዶ/ር ዋና ሌቃ፣ የትምህርት ሥርዓታችን ከስትራቴጂ እና ፖሊሲ ዝግጅት በዘለለ የጠራ ፍልስፍና ባለመኖሩ ምክንያት ጥራት መልስ ያላገኘ የዘወትር ችግር እንደሆነ ዘልቋል ይላሉ፡፡ ቴክኒክና ሙያ ከክልል ክልል፣ ከተቋም ተቋም የማይመሳሰልና ወጥነት የጎደለው የጥራትራ ደረጃ መከሰቱ ዘርፉ ሥልጠናውን ከማዳረስ በዘለለ በጠራ መርህ ላይ ተመስርቶ እየተተገበረ እንዳልሆነ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም የፖሊሲ አውጪዎችና ምሁራን ለዚህ ግዙፍ ሴክተር በምርምር የታገዘ ድጋፍ ሊያደርጉት ይገባልም ብለዋል ዶ/ር ዋና፡፡

participants

ፕ/ር ዳንኤል ቅጣው በመሩት በዚህ የፓናል ውይይት ከጀነራል ዊንጌት ፖሊ-ቴክኒክ ኮሌጅ እና ከፌደራል የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኢንስቲትዩት የተገኙ ተሳታፊ ተማሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መፍትሄ ያሉትን አስተያየት አቅርበዋል፡፡ ጥራትን ለማሳደግ መንግስትና የዘርፉ አመራር አካላት በየቦታው ተቋም ለመክፈት በሚደረግ ጥረት ብቻ ሳይገደቡ በሳይንሳዊ መረጃ ላይ የተደገፈ በቂ የሆነ የሥልጠና ቁሳቁስ አቅርቦት፣ ብቁ አሠልጣኝ እና የዘመነና ተግባራዊ የኢንዱስትሪ ትሥሥር እነዲዘረጋ አጥብቀው ሊሠሩ ይገባል በማለት ውይይቱ ተጠናቋል፡፡

የውይይቱን ቪዲዮ ማየት ከፈለጉ ይህንን ተጭነው ያገኙታል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *