የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የሥነ ጥበባት ማዕከል ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ተወያየ

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነጥበባት ማዕከልን የሥራ አድማስ በማስፋት የአገሪቱ የባህልና  የሥነ ጥበብ እንቅስቃሴዎች ላይ ሳይንሳዊ አበርክቶ  ለማድረግ በኪነጥበብ እና በባህል ዘርፍ ከሚሠሩ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አድርጓል.። 

የምክክር መድረኩን በእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ያስጀመሩት የአካዳሚው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ የሥነ ጥበባት ማዕከሉ በአዲስ አበባ፣ ጉለሌ ክፍለ ከተማ  የሚገኝ  በኢትዮጵያ ታሪክ በሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ ስመጥር ጸሐፊ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ደራሲ፣ የታሪክ ጸሐፊ፣ የስነ-ምግባር አስተማሪ የነበሩት የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ በቅርስነት የተመዘገበ መኖሪያ ቤትን አካዳሚው ከመንግሥት ተረክቦ በዋና ጽሕፈት ቤትነት እየተገለገለበት እንደሆነ ገልጸዋል።

የሥነ ጥበባት ማዕከሉ የታሪካዊ ቅርስነት ይዘቱ የተጠበቀና በተለያዩ  አገር በቀል እና መድኃኒትነት ባላቸው ተክሎች የተዋበ እንዲሁም በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ ምህንድስናና ሂሳብ (STEM) ማዕከልነት አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመው ታዳሚዎቹ በሚመቻቸው ሰዓት እንዲጎበኙትም ጋብዘዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአካዳሚው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጽጌ ገብረ-ማርያም በኪነጥበብ የበለጸጉ የትምህርት መርሐ ግብሮች ውስጥ የሚሳተፉ ወጣቶችና ሕፃናት የመማር ተነሳሽነታቸውን ከመጨመራቸው ባሻገር ለውጤታማ የባሕርይ መሻሻሎች ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አያይዘውም የትምህርት ዋነኛ ዓላማ የአንድን ግለሰብ ሁለንተናዊ እድገት ማረጋገጥ ሲሆን የሥነጥበብ ትምህርት ይህን ዓላማ ለማሳካት ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳለው አብራርተዋል።

የምክክር መድረኩ ዓላማ ካለፈው አፈጻጸም መልካም ልምዶችን ማስቀጠልና ክፍተቶች ማረም፣ በኮሮና (COVID-19) ምክንያት ተቀዛቅዞ የነበረው የሥነጥበባት ማዕከሉን እንቅስቃሴ አጠናክሮ ማስቀጠል፣ እንዲሁም በአገሪቱ የባሕልና የሥነ ጥበባት እንቅስቃሴዎች ላይ የአካዳሚውን ሳይንሳዊ አበርክቶ ለማሳደግ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በይበልጥ የማዕከሉን አገልግሎት ለሁሉም ተደራሽ እና አካታች ለማድረግ  እንዲሁም  ተቋማዊ ትስስር ለመፍጠር ያለመ መድረክ መሆኑንም  ፕሮፌሰር ጽጌ አብራርተዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ ስለ ማዕከሉ ታሪካዊ ዳራ እና ዓበይት ክንዉኖች ገለጻ ያደረጉት የቀድሞው የማዕከሉ ዳይሬክተር እንዳለጌታ ከበደ (ዶክተር)፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት በሥነ ጥበባት ማዕከሉ ውስጥ በተለያዩ የኪነ ጥበብ ዘውጎች የተዘጋጁ  ሥራዎች በወር ሁለት ጊዜ  ይካሄዱ እንደነበር  ገልጸዋል።

በማዕከሉ የተቋቋመው አነስተኛ ሙዚየም በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ፣ በልጆቻቸው እና በልጅ ልጆቻቸው የተጻፉ መጻሕፍት፣ ስለመጽሐፎቹ የተጻፉና የተጠኑ ድርሳናት፣ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ከንጉሠ ነገሥቱ፣ ከሹማምንቱ እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር የተነሷቸው ፎቶግራፎች እና የኅሩይን ሕይወት የሚገልፁ ቁሣቁሶች ይገኙበታል ብለዋል፡፡

በማዕከሉ የሥነ ጥበብ ባለሞያዎች የፈጠራ ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት፣ ዕውቀታቸውንና ክህሎታቸውን የሚያጋሩበት መድረክ ላይ የኢትዮጵያን እሴቷን፣ ታሪኳን፣ ባህሏን ኪናዊ በሆነ መንገድ የሚያስተዋውቁ፤ በሥዕል፣ በፊልም፣ በቴአትር፣ በድርሰት፣ በኪነ ቅርጽ፣ በፎቶግራፍ፣ በዳንስና በሌሎች የጥበባት ዘርፎች ዝንባሌ ያላቸው ጀማሪና አንጋፋ ሙያተኞች ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት፣ ልምድ የሚለዋወጡበትና በአጫጭር ስልጠናዎች የሚሳተፉበት ነው ብለዋል።

አያይዘውም አካል ጉዳተኞች በኪነጥበብ ዘርፍ ላይ ያበረከቱት አስተዋፅኦ የሚዘከርበትና የሚበረታቱበት መድረክ መሆኑን ዶክተር እንዳለጌታ አብራርተዋል።

የሥነጥበባት ማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ይታገሱ ጌትነት ማዕከሉ ወደ ፊት ሊሰሯቸ ያቀዳቸውን ተግባራት እና ለግቡ ሥኬት የባለድርሻ አካላት ሚና ምን መሆን እንዳለበት ገለጻ አድርገዋል።

የውይት መድረኩን የመሩት የማዕከሉ የስራ ቡድን ሰብሳቢ ሰዓሊ እና ቀራጺ አቶ በቀለ መኮንን በበኩላቸው የሳይንስ አካዳሚው የሥነጥበባት ሥራዎችንና አገር በቀል እውቀቶችን በሳይንሳዊ መንገድ ለማሳደግ እና ለማስቀጠል የሚያደርጋቸው ጥረቶች ተሳክተው የኪነ ጥበብ ዘርፍ ለአገር እና ለባለሙያዎች ሁለንተናዊ እድገት እንዲጠቅም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መሥራት አለባቸው ብለዋል።

በውይይቱም በሙዚቃ፣ በሥዕል፣ በድርሰት፣ በፋሽን ዲዛይን፣ በትወና እና ሌሎች ዘርፎች አንጋፋ የሆኑ  ባለሙያዎች እንዲሁም ከባህልና ስፖርት መሥሪያ ቤት የተውጣጡ እንግዶች ተሳትፈዋል።

ተሳታፊዎች  በቀረቡ ሐሳቦች ዙሪያ  ባነሷቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች የኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ሥራዎች በዘመናት መካከል የመድመቅና መልሶ የመደብዘዝ ዋናው ችግር ‘’በሳይንሳዊ መንገድ ባለመመራቱና መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ  በመሆኑ እንደሆነ በመጥቀስ፤  ዘርፉን መልሶ ማጠናከር የቤት ሥራችን ነው ብለዋል።

በዕለቱ በቀረቡ ምክረ ሃሳቦችን መነሻ በማድረግ የሥነጥበብ ማዕከሉ በቀጣይ በሚሰራቸው ሥራዎች ከባለድሻ አካላት ጋር በጥምረት በትግግዝ ለመስራ ዝግጁ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ለአካዳሚው እና ለሙያው ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያላቸውን ሥራዎች በመሥራት ሀገር ተጠቃሚ እንድትሆ እንደሚሠራ ተነግሯል።