የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ መታሰቢያ የፎቶ አውደ ርዕይ እና የሙያዊ ውይይት መድረክ ተካሄደ

በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ስም የተሰየመው የሥነ ጥበባት ማዕከል የእውቁን ደራሲ፣ ዲፕሎማት እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የነበሩትን የክቡር ብላቴን ጌታ ኅሩይ መታሰቢያ የታሪካዊ ፎቶግራፍ አውደ ርዕይ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት እና ‘‘የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ሕይወትና ሥራዎች’’ በሚል ርእስ ውይይትአካሂዷል።

የአካዳሚው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ  የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር አድርገዋል።

ቅዳሜ መስከረም 14/2015 ዓ.ም፣ በርካታ ታዳሚዎች በተገኙበት አውደ ርዕዩ በይፋ ያስጀመሩት የአካዳሚው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጽጌ ገብረማርያም ስለ አካዳሚው እና ዝግጅቱ አጠር ያለ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የዝግጅቱ ዓላማ ክቡር ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴን የዕረፍት መታሰቢያን ማዕከል በማድረግ ሥራዎቻቸውን ለመዘከር፣ በሥማቸው በሚጠራው ማዕከል ሥር የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶችን ለመጠገን የመነሳሻ አውድ ለመፍጠር እንዲሁም ቋሚ ተጨማሪ ቅርስ የሚሆን አሻራን ለማኖር የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎችን ለማስጀመር ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ፕሮፌሰር ጽጌ አሳውቀዋል፡፡

የፎቶግራፍ አውደ ርዕዩ በይፋ ተከፍቶ ጉብኝት ከተከናወነ በኋላ በፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ አወያይነት፣ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ የብላቴን ጌታ ኅሩይን ሕይወትና አበርክቶ የሚዳስስ ለውይይት መነሻ  የሚሆን ገለጻ አቅርበዋል፡፡ 

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ለሀገራቸው ሁለንተናዊ ሥልጣኔና ዕድገት መሻሻል የራሳቸውን አሻራ ጥለው ያለፉ ታላቅ ምሁር ስለነበሩ፤ በትውልድ ዘንድ አበርክቷቸው ሲታወሱ እንዲኖሩ ለስማቸው ማስታወሻ እንዲሆን ጥንታዊ መኖሪያ ቤታቸው የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ  ዋና ጽ/ቤት ሆኖ በማገልገል ላይ እንደሚገኝ ፕሮፌሰር ማስረሻ ገልጸዋል።

ፕሮፌሰር ባህሩ ባቀረቡት ገለጻ ብላቴን ጌታ ኅሩይ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ታዋቂ ዲፕሎማት፣ ደራሲና የግብረገብ መምህር የነበሩ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡ ኅሩይ በጥንታዊ የሀገር በቀል ዕውቀቶችና  በዓለማቀፋዊ ጉዞና ንባብ የተቀረጹ  እንደነበሩም አውስተዋል፡፡

የሰለጠኑ ሀገራትን ስልጣኔና መልካም ልምዶችን ለመቅሰም ካላቸው ጉጉት የተነሣ አዲስ አበባ  በሚገኘው የስዊድን ሚሽን ትምህርት ቤት ገብተው የእንግሊዝኛ ቋንቋ መማራቸውንም ጠቅሰዋል። ከእንግሊዝኛ በተጨማሪም የዐረብኛ ቋንቋን ለማጥናት ሞክረው እንደነበር ፕሮፌሰር ባህሩ ተናግረዋል፡፡