የሥነ ሕዝባዊ ትሩፋት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ጅምር የልማት እንቅስቃሴዎችን ማጠናከርና ምቹ ፖሊሲዎችን ቀርጾ መተግበር ይገባል

ኢትዮጵያ የሕዝብ የእድሜ አወቃቀር ሽግግርን ተከትሎ ሊመጣ የሚችለውን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ወይም ሥነ ሕዛባዊ ትሩፋት ዕውን ለማድረግ የሚያስችላት የልማት ጉዞ ጅምሩ የተመቻቸ መሆኑን በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚና በጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ ትብብር በመካሄድ ላይ ያለው ጥናት አመለከተ፡፡

ሥነ ሕዝባዊ ትሩፋት በሕዝብ የእድሜ አወቃቀር ለውጥ ማለትም በሰራተኛ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች (15-64 ዓመት) ቁጥር ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታችና ከ64 ዓመት በላይ ከሆኑ ሰዎች ቁጥር በልጦ ሲገኝ የሚፈጠር እድገት የዕድል መስኮት ነው፡፡ የዚህን በጊዜ የተገደበ ዕድል ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ደግሞ የተቀናጀ የዘርፎች የልማት ጉዞ በተለይም ዋና ዋና ተብለው በሚጠቀሱት በጤና፣ በትምህርት፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በሴቶች ተጠቃሚነትና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ አጠናክሮ መስራትና ምቹ ፖሊሲዎችን መቅረጽ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል፡፡

ጥናቱ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ በተለይ በህጻናትና እናቶች ጤና አበረታች ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን እና ከዚህ በተጨማሪም በቤተሰብ ምጣኔ፣ በትምህርት በተለይ ደግሞ በልጆችና ልጃገረዶች የትምህርት ተሳትፎ የተሰጠው ትኩረት በአንጻራዊ መልኩ አወንታዊ ውጤትን እያስመዘገበ ይገኛል፡፡

በአሁኑ ወቅት ያለውን ከፍተኛ ወጣት የህብረተሰብ ክፍል በተለይ ደግሞ ሴቶችን በተለያዩ ሙያዎች ማሰልጠንና ክህሎት እንዲኖራቸው ማድረግ ከዚሁ ጋር በተያያዘም ጠቃሚና ምርታማ በሆኑ የሥራ ዘርፎች ላይ ማሰማራት የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን ቀርጾ መተግበር ሥነ ሕዝባዊ ትሩፋትን በተገቢው መልኩ ዕውን ለማድረግ ቁልፍ መፍትሄ መሆኑን ጥናቱ አበክሮ አስገንዝቧል፡፡

ጥናቱ የማክሮ ኢኮኖሚ እና ፊሲካል ፖሊሲዎች ትግበራ የኢንቨስትመንት ሁኔታዎችን በሚያጎለብቱና ከፍተኛ የሰው ኃይል የስራ ስምሪትን የሚያበረታቱ መሆን እንደሚገባቸው ይመክራል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የህግ የበላይነትን የሚያጎለብቱ የመልካም አስተዳደር ስርአት መዘርጋት፣ ሙስናን በተጠናከረ መልኩ መዋጋትና በመንግስት፣ ሲቪል ማህበራት እና በህዝቡ መካከል ያለውን ቅንጅት ማጠናከር ተገቢ መሆኑን ጥናቱ አስገንዝቧል፡፡

በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚና በጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ ትብብር የተካሄደው ይህ ጥናት ተጠያቂነትና የአሰራር ግልጽነት በሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚሰፍንበትንና የሚፈተሽበትን ተገቢ አሰራር ማጠናከር ሁሉን አቀፍ ዕድገት በአገሪቱ በዘላቂነት ለማስፈን ቁልፍ ጉዳይ መሆኑንም አመልክቷል፡፡

በተጨማሪም ጥናቱ የሁለተኛ ደረጃ፣ መደበኛ ያልሆነና የጎልማሶች ትምህርት ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት የሚገባ መሆኑን አመልክቷል፡፡

————————————————————————————————————–

የጥናቱ ሪፖርት በተለያዩ ዘርፎች የሚገኙ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት የተውጣጡ፣ ፖሊሲ አውጭዎች፣ ፕሮግራም አስፈጻሚዎች፣ ተመራማሪዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

የጥናት ሪፖርቱን ለማግኘት ይህን ይጫኑ፡፡

ውይይቱን ለማግኘት ይህን ይጫኑ፡፡

Demographic Dividennews brief English Final

Demographic Dividend Effort Index Report – Ethiopia