የምርምርና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሴቶች መማማሪያ መድረክ

የኢትዮጵያ ሴቶች መማማሪያ መድረክ  መጠናከር በከፍተኛ ትምህርትና በምርምር ተቋማት ደረጃ ሴቶችን በማብቃት እና ወደ አመራር በማምጣት ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ከዓለምአቀፍ ሣይንስን የማምጠቅና ፖሊሲ መረብ /International Network for Advancing Science and Policy (INASP)/ የተሰኘና  ተቀማጭነቱ ለንደን ከሆነው ድርጅት ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ የሥርዓተ ጾታ መማማሪያ መድረክ የሥርዓተ ጾታ አሸናፊዎች /Gender Champions/ በሚል ርዕስ ከጥቅምት 2-4 /2014 ዓ.ም. የሦስት ቀናት ዓውደ ጥናት በአሰላ ከተማ በሚገኘው የአርሲ ዩኒቨርስቲ አስተናጋጅነት ተካሂዷል፡፡

በዓውደ ጥናቱ የመክፈቻና የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ያስተላለፉት የአርሲ ዩኒቨርስቲ አካዳሚክስ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ቃሲም ኪሞ ዩኒቨርሲቲው የሥርዓተ ፆታ እኩልነትንና ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ የሴቶችን ፎረም  የመደገፍና የማጠናከር ሥራዎች ይሰራሉ ብለዋል።

የአካዳሚው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ በዓውደ ጥናቱ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር የዓውደ ጥናቱ ዋና ዓላማ የሥርዓተ ፆታ እኩልነትንና ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ፤ እንዲሁም በዚህ ረገድ የሚደረጉ ተቋማዊ ጥረቶችን ለመደገፍና ለማሳደግ ያለመውን የምርምርና ከተኛ ትምህርት ተቋማት የሥርዓተ ፆታ መድረክ በሚመለከት ያለውን ግንዛቤ ማስፋት መሆኑን ተናግረዋል።

አአካዳሚዉ የሥርዓተ ጾታ እኩልነት በምርምር እና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የማረጋገጥ አስፈላጊነትን ግንዛቤ ለማሳደግ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

የአአካዳሚዉ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር የዓለምፀሓይ መኮንን እንደገለጹት ዓውደ ጥናቱ አካዳሚው ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባና በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ካዘጋጃቸው ቀጣይ ሲሆን በተለያዩ የሙያ መስኮች የተሰማሩ ሴት ምሁራንን በማሰባሰብ ተሳትፎአቸውንና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በመወያየት ችግሮቻቸውን የመፍታትና የግንባር ቀደምነት ሚናቸውን በተገቢው መንገድ ለመወጣት የሚችሉበትን ልምድ እንዲለዋወጡ ለማስቻል ታስቦ የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡

አያይዘውም ዓውደ ጥናቱ  ላይ ከተለያዩ የምርምርና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡ 26 ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን በ“ሥርዓተ ጾታ ዙርያ የሚስተዋሉ የተዛቡ አመለካከቶችንና የቃላት አጠቃቀምን ማስተካከል” እና “በተቋማት የሥርዓተ ፆታ አድሏዊነትንና ኢፍትሐዊነትን ለመታገል የሚያስችል ስትራቴጂ መንደፍ” በሚሉና ሌሎች በርካታ ተዛማጅ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የውይይት ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እንደተደረገባቸው አብራርተዋል።

በተጨማሪም የአውደ ጥናቱ በዩንቨርሲቲው መካሄድ አካዳሚውና ዩኒቨርስቲዉ በጋራ ጉዳዮች ላይ ተቀራርበው ለመሥራት እንዲችሉ በር ከፋች እንደሆነም ፕሮፌሰር የዓለምፀሓይ ገልጸዋል፡፡

የአርሲ ዩኒቨርስቲ የአስተዳደር  ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሜሮን በበኩላቸው ዓውደ ጥናቱ ሴቶች በተናጠል ሥራቸውን ከማከናወን ይልቅ በተደራጀና በተጠናከረ መልኩ ማከናወን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሚረዳ ግንዛቤ ያሳደገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዓውደ ጥናቱ ወጪዎች በአካዳሚውና በተባባሪው ድርጅት የተሸፈነ ሲሆን አርሲ ዩነቨርስቲ ደግሞ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ የኢንተርኔትና ሌሎች ተጓዳኝ አገልግሎቶችን በመስጠት ድጋፍ አድርጓል፡፡ ለዚህም አካዳሚው ከፍ ያለ ምስጋና ያቀርባል፡፡