ዓለም አቀፍ የአእምሯዊ ንብረት ቀን ተከበረ

የዘንድሮውን ዓለም አቀፍ የአእምሯዊ ንብረት ቀን “አእምሯዊ ንብረትና ወጣቶች፥ ፈጠራ ለተሻለ ነገ” በሚል መሪ ሐሳብ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ከኢትዮጰያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን  እና ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የፈጠራ ሥራዎች ዓውደ-ርዕይና በፓናል ውይይት በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ቅጥር ግቢ  በድምቀት ተከብሯል።

ጠበቃ፣ የህግ አማካሪና አስልጣኝ የሆኑት አቶ ቶማስ ገብረሚካኤል የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር ለወጣቶች የፈጠራ እና የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት በማስመልከት አውደ ጥናት አቅርበዋል፡፡

ዶክተር ትዕግሥት ደሱ ‘‘የአእምሯዊ ንብረት ትመናና ፋይናንሲንግ’’ በተሰኘ ርዕስ በዓውደ ርዕዩ ሁለተኛውን ጽሑፍ ያቀረቡት ሲሆን ሐሳብ በማመንጨት የፈጠራ ስራ ለሠሩ ባለመብቶች የአእምሯዊ ንብረት እሴቶቻቸውን በመተመንና እንደ ማስያዥያ

 በመጠቀም ብድር ማግኘት የሚያስችላቸውን የፖሊሲና የአሠራር መገምገም ላይ ያጠነጠነ እንደነበር ተብራርቷል፡፡

በፓናል ውይይቱ ላይ የመንግሥት የስራ ሃላፊዎች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን፣ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ኃላፊዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት ተወካዮች፣ ወጣት ኢንቬንተሮችና የሥራ ፈጣሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ የዝግጅቱ ዓዉደ ርዕይም ከሚያዝያ 20 /2014 ዓ.ም እስከ 21/2014 ዓ.ም ድረስ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ለጎብኚዎች ክፍት ሆኖ ቆይቷል።

በታዳጊና በወጣት የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎችና ተመራማሪዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ሦስቱ ተቋማት በጋራ ባዘጋጁት በዚህ ዝግጅት ላይ 62 ፕሮጀክቶች ለእይታ ቀርበው ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ የቀረቡት ስራዎች ታዳጊዎቹና ወጣቶቹ አመቺ ሁኔታዎች ከተፈጠሩላቸው ድንቅ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለማህበረሰብ የማቅረብ እምቅ አቅም ያላቸው መሆኑን ያሳዩ ናቸው፡፡

በዓውደ ርዕዩ ላይ በክብር እንግድነት ተጋብዘው ንግግር ያደረጉት የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ ባስተላለፉት መልዕክት አእምሯዊ ንብረት የልማት መሳሪያ እንዲሆን ዓለም አቀፋዊ እና ሀገራዊ የዕድገት ደረጃዎችን ያማከለ የአእምሯዊ ንብረት ፖሊሲን የማዘጋጀትና ተግባራዊ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል። አያይዘውም የሀገሪቱን ችግሮች ለሚፈቱ የፈጠራ ሥራዎች ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት እንዳለበት ጠቁመው በዚህ ረገድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል  አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤርምያስ የማነብርሀን በበኩላቸው የወጣቶች የፈጠራ ሥራዎች እንዲጠናከሩና ለአገሪቱ ሁለንተናዊ ልማት የሚኖራቸው አስተዋፅኦ እንዲጎለብት የተጠናከረ የአእምሯዊ ንብረት ስርአት መኖር  ወሳኝ መሆኑን በመግለፅ ለዚህ ስኬት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ ተቋማቱ በቅንጅት መሥራታቸው እምቅ አቅም ያላቸውን ወጣቶች ወደፊት ለማምጣት እና ለማበራከት እንደሚረዳ ገልጸው አካዳሚው ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ልማት ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዝግጅቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አብርሃ ወልደዮሀንስ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ልማት ለሀገር እድገት ለሚያበረክተው ቁልፍ ድርሻ አፅንኦት የሰጡ ሲሆን ለወጣት የኢኖቬሽን ተዋንያንና ለሥራ ፈጣሪዎች ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የዓለም አእምሯዊ ንብረት ቀን ‘‘World Intellectual Property Day (WIPD)’’ን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው ዓውደ ርዕይ ላይ የቀረቡትን የፈጠራ ሥራዎች በማወዳደር ደረጃ የተሰጣቸው ሲሆን ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ በመያዝ ላሸነፉት የፈጠራ ባለመብቶች ኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል ሽልማት አበርክቶላቸዋል፡፡

በመዝጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት በኢትዮ ቴሌኮም የኮርፖሬት ዘርፍ ቺፍ ኦፍ ስታፍ አቶ መሳይ ውብሸት ድርጅታቸው በኢትዮጵያ ለቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ልማት ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ ከሚገኙ ተቋማት አንዱ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም የወጣቶችን የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን  እንቅስቃሴ ለማበረታታት ተግቶ እንደሚሠራ  ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ  በበኩሉ ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ደረጃ አሸናፊ ለሆኑ ተወዳዳሪዎች የኢንተርፕርነርሺፕ እንዲሁም የፈጠራ ስራዎቻቸውን ወደ ተግባር ለመለወጥና ወደ ገበያው ለመግባት የሚያስችላቸውን የቢዝነስ ዕቅድ አዘገጃጀት ስልጠና እንደሚያመቻችላቸው በማጠናቀቂያ መርሃ ግብሩ ላይ ተገልጻል፡፡ ለሌሎች የፈጠራ አቅራቢዎቹ የእውቅና ሰርተፍኬት በመስጠት እንዲሁም እምቅ የፈጠራ ችሎታ ያላቸውን ታዳጊዎችና ወጣቶች ለማበረታታት መሰል ዝግጅቶች ወደፊት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በመግለጽ አውደ ርዕዩ በይፋ ተጠናቋል።