ዐጀሚ ሥነጽሑፍ  በኢትዮጵያ ታሪክና ሥነጽሑፍ ውስጥ

በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የብላቴን ጌታ  ኅሩይ  ወልደሥላሴ  የሥነጥበባት  ማዕከል አዘጋጅነት  ዐጀሚ ሥነጽሑፍ በኢትዮጵያበሚል ርዕስ ውይይት ተካሄደ፡፡

የውይይቱ ዓላማ ዐጀሚ ሥነጽሑፍ  በኢትዮጵያ ታሪክና ሥነጽሑፍ ውስጥ ያለውን ቦታ በማስረጃ በማስደገፍ መረጃ መስጠትና ማስተዋወቅ መሆኑን በዝግጅቱ ላይ ተገልጿል።

ገለጻና ውይይቱን ያደረጉት አቶ ሐሰን ሙሐመድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዐረብኛ ቋንቋ ትምህርት ክፍል መምህርና የትምህር ክፍሉ ኃላፊ ሲሆኑ  በዘርፉ ላይ ሦስተኛ ድግሪያቸውን በመስራት ላይ ይገኛሉ።

አቶ ሐሰን ዐረብ ያልሆኑና የሌላ ቋንቋ ተናጋሪዎች ዐረብኛ ፊደላትን ተጠቅመው ሲጻፉ የቆዩ መሆናቸውን ጠቅሰው በዚህ የአጻጻፍ ዘዴ ያፈሯቸው የጽሑፍ ቅርሶች ዐጀሚ ተብለው እንደሚጠሩ አብራርተዋል። ከቅኝ  ግዛት ዘመን አስቀድሞ የአፍሪካና የእስያ ሕዝቦች፣ ቋንቋቸውን በዐረብኛ ፊደል በመጠቀም የታሪካቸው፣ የባህላቸውና የሥነጽሑፋቸው መግለጫ መሣሪያ በመሆን ማገልገሉንም ገልጸዋል።

ይህም በቅድመ ቅኝ ግዛት የአፍሪካ ማህበራዊ እውቀቶች  በተወሰ መጠን ቢሆንም በጽሑፍ የተሰነዱ እንደነበሩ ያመላክታል።

በሀገራችን ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ዘንድ በብዛት የሚታወቀውና በተለያዩ ቋንቋዎች ለሕዝብ የሚደርሱ መንዙማዎች ውስጥ እጅግ ታዋቂ የሆኑት ሥነ ጽሑፋዊ ይዘታቸው አስቀድሞም  በዐጀሚ የተጻፉና በከፊልም በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞና በሌሎች ሀገርኛ ቋንቋዎች የተደረሰ መሆኑን  አቶ ሐሰን አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ የዐጀሚ ጽሑፍ የተጀመረበትን ወቅት የሚገልጽ መረጃና ቁርጥ ያለ ምላሽ ለጊዜው ባይገኝም፣ በግለሰቦች እጅና በተለያዩ ቤተመዛግብት የሚገኙት ድርሳናት ከመካከለኛው ክፍለ ዘመን አንስቶ የነበረና ከ18ኛው ክፍለ ዘመን በኋላ በስፋት የተጻፉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በሀገራችን በዐጀሚ የተደረሱ የጽሑፍ ቅርሶች በብዛት የተጻፉና ይዘታቸውም በአብዛኛው በሐይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ቢሆንም ዘርፈ ብዙ ማኅበራዊ ጉዳዮችንም ያካተተ ነው፡፡

በእስልምና ሐይማኖታዊ ተቋማት የተማሩ ኢትዮጵያውያን በዐረብኛ ቋንቋ፣ በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ፣ በሐረሪና በሌሎች የሀገሪቱ ቋንቋዎች የዐረብኛ ፊደሎችን በመጠቀም ድርሳናትን እየጻፉ ሥነጽሑፋዊ ቅርሶችን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲያስተላልፉ መቆየታቸውን አክለዋል፡፡

በርከት ያሉ የመንዙማ፣ የታሪክ መጽሐፍትና ሌሎች ጽሑፎች በኢትዮጵያውያን የእስልምና ሃይማኖት ሊቃውንት የተደረሱት ከምዕተ ዓመታት በፊት ነበር፡፡ አጥኚው ባቀረቧቸው የሰነድ መረጃዎች፣ በዐጀሚ ከተጻፉት ቋንቋዎች አማርኛ፣ ትግርኛ፣ ሐደርኛ፣ አርጎብኛ፣ ስልጥኛና ወለንኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ አፋርኛና ሶማልኛ ይገኙባቸዋል፡፡

የዐጀሚ ጽሑፍ የተጻፈባቸው በርካታ ሀገር በቀል ቋንቋዎች መገኘታቸውንና የሥነ ጽሑፉ  ከሐይማኖታዊና መንፈሳዊ ጉዳዮች በተጨማሪ የተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮችን ማለትም የጋብቻ ሥርዓትን፣ የንግድ ግንኙነትን፣ የሕዝብ አስተዳደርን ወዘተ በብዛት እንደሚዳስስ መምህር ሐሰን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነጥበባት ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ይታገሱ ጌትነት በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ የዐጀሚ ሥነ ጽሑፍን በተመለከተ በማኅበረሰባችን ዘንድ ያለው ዕውቀት ውስን በመሆኑ ለረዥም ዘመናት ትኩረት ሳይሰሰጠው መቆየቱን አብራርተዋል።

በመጨረሻም በብዙኅን ዘንድ የማይታወቁ ትኩረት ያልተሰጣቸው የሀገሪቱ ሥነጽሑፋዊ ሀብቶች እንዲታወቁና እንዲጠበቁ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ አካዳሚው እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡