‹‹ወደኋላ›› የተሰኘ የማህሙድ ዳውድ ፊልም ላይ ውይይት ተደረገ

‹‹ትውልዱን ከዕውቀት እና ታሪክ ባርነት በማላቀቅ ከራሱ ከቀደመው ታሪኩና ዕውቀት ምንጮቹ ማስታረቅ ያስፈልጋል›› ደራሲና ዳይሬክተር ማህሙድ ዳውድ

 

በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሥር የሚገኘው የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነ ጥበባት ማዕከል በየ15 ቀኑ በሚያደርገው የጥበብ ውሎ 58ኛው መርሐ-ግብሩ ዛሬ ሐምሌ 20/2011 ዓ.ም. በማህሙድ ዳውድ ተደርሶ በተዘጋጀው ‹‹ወደኋላ›› በተሰኘ ፊልም ላይ ውይይት አደረገ፡፡

‹‹ወደኋላ›› ፊልም አብዛኛው የኢትዮጵያ የዕውቀትና የምርምር ሥርዓት ከቀደመው አገራዊ ዕውቀት የተነጠለ በመሆኑ ‹የዕውቀት ባርነት› ቅርቃር ውስጥ በመግባቱ ተጨባጭ አገራዊ ለውጥ ማምጣት አልቻለም፤ በመሆኑም የዘመናዊ ትምህርትና የዕውቀት ግንባታ ሥርዓታችን በጥልቀት መፈተሽ እንዳለበት የሚናገር ታሪክ የያዘ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ከተጀመረ ከ100 ዓመት በላይ የሆነው ቢሆንም፣ በዚህ ዘመናዊ ትምህርት የተማሩ አካላት የቀሰሙት ዕውቀት በተግባር ተፈትሾ የአገርና የኅብረተሰብን ችግር በተሟላ መልኩ መቅረፍ አልቻለም ይላል ማህሙድ፡፡

እንደ ፊልሙ ደራሲና ዳይሬክተር አባባል ‹‹የምንማረው በተግባር ኅብረተሰባችን የሚፈልገውን ቴክኖሎጂም ሆነ የፈጠራ ሥራዎች አምርተን ከችግር ለማላቀቅ ካልረዳ፣ በዓለም ገበያ ተቀባይነት ያለው ምርት ካላቀረብን፣ ዘወትር ተቀባይና ገዢ ብቻ የምንሆን ከሆነ እንደ ኅብረተሰብ ልንለወጥ አንችልም›› በማለት በአንፃሩ የቀደመው ትውልድ የራሱን  የምርምር ሥራ ሠርቶ የዕውቀት ሥርዓት ገንብቶ እንዳለፈ በስፋት አብራርቷል፡፡

በውይይቱም ደራሲና ዳይሬክተር በሠራቸው የፊልም ሥራዎች የሚቀርፃቸው ሴት ገጸ-ባህሪያት ጥንካሬ የተላበሱ በመሆናቸው ለዚህ ያለው ዕይታን አስመልክቶ ጥያቄ ቀርቦለት፣ ‹‹እኔ የማውቃቸው ኢትዮጵያውያን አርበኞች፣ አገር መሪዎች እና በራሳቸው የሚቆሙ ሴቶችን ነው፤ በሥራዎቼም የማቀርበው እነዚህን ነው›› በማለት በፊልም ሥራ ውስጥ የተዛነፈ ሥርዓተ-ፆታ አረዳድን ማረም እንደሚገባ ተናግሯል፡፡

ደራሲና ዳይሬክተር ማህሙድ ከ‹ወደኋላ› ፊልም በፊት ‹እቴጌ›፣ ‹ሼፉ 1›፣ ‹ያነገስከኝ›፣ ‹ነፃ ትግል›፣ ‹ምንሼ›፣ እና ‹ሳማሎ› (ኦሮምኛና አማርኛ) ድርሰትና ዝግጅቱን፤ እንዲሁም ‹አሜን›፣ ‹ትራፊኳ› እና ‹አየሁሽ›ን የድርሰት ሥራውን አዘጋጅቶ ለዕይታ ያበቃ ወጣት ፊልም ባለሙያ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *