እጅግየተከበሩየዓለምሎሬትሜትርአርቲስትአፈወርቅተክሌሥነጥበባዊሥራዎችላይሂሳዊውይይትተካኼደ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የሥነ ጥበባት ማዕከል ጋር በመቀናጀት እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌን የሥነ ጥበብ ሥራዎች የሚዳስስ ሂሳዊ ውይይት በአካዳሚው ቅጥር ግቢ በዘርፉ ምሁራን ተደርጓል፡፡

የመድረኩን መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሠርፀ ፍሬ ስብሐት የሂስ ባህል መጎልበት ለኪነ-ጥበብ እድገት ወሳኝ መኾኑን ገልጸው በኪነ ጥበብ ሥራዎች ላይ ሂስ የመስጠት እና ውይይት የማድረግ ባህል በሚፈለገው ደረጃ አለመዳበሩን አመላክተዋል፡፡

አያይዘውም “ሂስ እና የሥነ ጥበብ ክዋኔ፣ የማይነጣጠሉ መኾናቸውን” ጠቁመው፤ “ሂስ በልኬት መመዘኛ አማካኝነት አንድን ሥነ ጥበባዊ ሥራ የሚፈክር (የሚተነትን) የሚያስተዋውቅ፣ አድናቆትና የማሻሻያ አስተያየቶችን መስጠትና መቀበልን የሚያለማምድ ሙያዊ ምዘና በመሆኑ ሥነ ጥበባዊ ልምምድን ወደ ዕውቀት የሚያሸጋግር ምሁራዊ ተግባር ነው” ሲሉ  ሂስ ለሥነ ጥበብ እድገት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አያይዘውም ሂስን በተሳሳተ አረዳድ ከነቀፋ ወይም ከውዳሴ ጋር ብቻ የማያያዝ ልምድ መኖሩን ገልጸው፤ ሀያሲያን በኪነ ጥበባት ሥራዎች ላይ የሚሰጡት ሂስ በኹለት መስመር ጽሑፍ ውስጥ ያልተካተቱ ጠቃሚ ሐሳቦችን የያዘ ሦስተኛ መስመር የመጠቆም ጥበብ መኾኑን እና  የሂስ ባህል መጎልበት ለኪነ ጥበብ እድገት የማይተካ ሚና እንደሚጫወት አብራርተዋል፡፡

አቶ ሠርፀ አክለው የሂስ ባህል እንዲጎለብት የዘርፉ ምሁራን እና የመገናኛ ብዙሃን ሚና  ከፍተኛ መኾኑን ጠቅሰው ድርጅታቸው በተለያዩ የሥነ ጥበብ ሥራዎች ላይ የሂስ መድረኮችን ሲያመቻች መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

ለተሳፊዎች የእንኳን ደህና መጣችኹ መልእክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ አካዳሚው በሥነ ጥበባት ማዕከሉ  በወር ሁለት ጊዜ ቅዳሜ ከሰዓት በተለያዩ  በሥነ ጽሑፍ፣ በሥነ ሥዕል፣ በፊልም፣ በቴአትር፣ በሙዚቃ እና በክወናዊ ጥበባት ላይ ያተኮሩ በርካታ የውይይት መድረኮችን ሲያካሂድ መቆየቱን ለተሳታፊዎች ገልጸዋል።

በዕለቱ፤ የሥነ ጥበብ ሃያሲና መምህሩ ሠዓሊ እሸቱ ጥሩነህ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የሥነ ጥበባዊ ሥራዎች ላይ ሙያዊ ገለጻና ሂሳዊ ምልከታቸውን አቅርበዋል።

በገለጻቸው ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ እና ሌሎች ተማሪዎች በ1940 ዓ.ም ለከፍተኛ ትምህርት ተመርጠው በምሕንድስና እና ሌሎች ዘርፎች ትምህርታቸውን ለመከታተል ወደ እንግሊዝ ሀገር ሲላኩ በስንብት ወቅት ንጉሠ ነግሥቱ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ “ተግታችሁ አጥኑ፣ ተማሩ ጠንክራችሁ መሥራት እና ሀገራችሁ ኢትዮጵያን የምትገነቡበትን ዕውቀት ይዛችሁ ተመለሱ፤  ስትመለሱ አዕምሯችሁ ዝግጁ የሆነ እውቀታችሁም ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚችል ጥበብን ሸምቶ እንዲመለስ  እንጂ አውሮፓ ውስጥ እንዴት ያሉ ረዣዥም ፎቅ ቤቶች እንዳሉ ወይም መንገዶቻቸው የቱን ያህል ስፋት እንዳላቸው እንድትነግሩን አይደለም” ሲሉ እንዳሳሰቧቸው አስታውሰዋል።

አፈወርቅ ተክሌ ገና በሕጻንነት ዕድሜያቸው የተመለከቱት የኢጣሊያ የግፍ ወረራ ያስከተለው የሰው፣ የንብረት እና የባህል ጥፋት በፈጠረባቸው ቁጭት እና በንጉሠ ነገሥቱ ወኔ ቀስቃሽ ምክር ሀገራቸውን ከነጻነት በኋላ እንደገና እንዴት መገንባት እንደሚቻል ሲያወጡ እና ሲያወርዱ ከቆዩ በኋላ ዋናው እና ቀዳሚው ጉዳይ እውቀት መሸመት መሆኑን ስለተረዱት ትምህርታቸውን በደንብ ቀስመው መመለስ ላይ እንዳተኮሩ አትተዋል።

በትምህርት  ቆይታቸውም በቀለም ቅብ፣ በቅርጻ ቅርጽ እና በኪነ ህንጻ ጥናቶች ላይ በመስራት ተመርቀው ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሱ እና “ዛሬ የምንሠራው ሥራ የዛሬን ሕይወት እያንጸባረቀ ለነገው ትውልድ ፈር መቅደድ አለበት፡፡” በሚል መርህ በተለያዩ ግዛቶች በመዘዋወር በአንዳንድ ቦታም እስከ ሦስት ወራት በመቀመጥ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባህልና ወግ አጥንተው ለዓለም ያስተዋወቁ መኾናቸውን ሰዓሊ እሸቱ አብራርተዋል።

ለሀገር ካበረከቷቸው ዘርፈ ብዙ ሥራዎቻቸው በተጨማሪ ጨረቃ ላይ ስማቸው ያጻፉ እና የሀገራችንን ሰንደቅ ዓላማ  አብረው ያሰቀሉ ብሔራዊ ኩራታችን ናቸው ሲሉም በአድናቆት ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ ሥነ ጥበብ እና ዲዛይን ትምህርት ቤት ኃላፊ፣ ሠዓሊ አገኘሁ አዳነ እና የእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የሥነ ጥበብ ክፍል መምህርና ሠዓሊ ኃይሉ ክፍሌ በሂሳዊ ገለጻው ከቀረቡ ሐሳቦች ዋና ዋና ነጥቦችን በማስታወስ ውይይት እንዲካሄድበት አድርገዋል።

በዚህ መሠረት ተሳታፊዎች የቀረበው ሂሳዊ ገለጻ የኪነ ጥበብ ዘርፉን ለማሳደግ ጠቃሚ መኾኑን ገልጸው፤ ይኽንኑ ለማጠናከር ላነሡት አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ምላሽ ተሠጥቶባቸዋል፡፡

የውይይት መድረኩን በመዝጊያ ንግግራቸው ያጠቃለሉት በአዲስ አበባ ምክር ቤት የዘርፉ ቋሚ ኮሚቴ አባል እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ክፍል መምህርት የተከበሩ ዶክተር አጋረደች ጀማነህ ቢሮው የኪነ ጥበብ ዘርፍን ለማሳደግ ከሥነ ጥበብ ማሠልጠኛ ተቋማት እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ለመሥራት የጀመረውን ግንኙነት አጠናክሮ እንዲቀጥል አበረታተዋል።

በመድረኩ የሙያ ማኅበራት አመራሮች፣ የሥነ ጥበባት ተማሪዎች፣ የሚዲያ ባለሙያዎች እና የቋሚ ኮሚቴ አባላት እና ከሳይንስ አካዳሚው ዘርፉ የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።