ግንቦት 11 ቀን 2014 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር የሥነ ጥበባት ዘርፍን በኢትዮጵያ በጋራ ለማሳደግ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ /MoU/ ተፈራረሙ።
የመግባቢያ ሰነዱን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኪነ ጥበብ ሥነ ጥበብና ፈጠራ ልማት ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ ወ/ሮ ነፊሳ አልመሃዲ እና የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ ተፈራርመዋል፡፡
ፕሮፌሰር ተከተል በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሁሉንም የሳይንስ ዘርፎችን ያቀፈ፣ የሳይንስ እዉቀትና ባህልን በማኸዘብ የኅብረተሰቡ ሕይወት እንዲሻሻል በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸው ስምምነቱ የሥነ ጥበባት ዘርፎችን የበለጠ ለማሳደግ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡
ሁለቱ ተቋማት ተቀናጅተው በመሥራት የኪነ ጥበብ እና ሥነ ጥበብ ዘርፉን በሳይንሳዊ መንገድ ለማሳደግ እና ብቁ የሆኑ ባለሙያዎችን ከማፍራት አኳያ ስምምነቱ ትልቅ አስተዋፆ እንዳለው ወይዘሮ ነፊሳ አልመሃዲ ተናግረዋል።
ስምምነቱ የፈጠራ ጥበባትን ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ፤ በባህል እና ኪነ ጥበብ ዙሪያ የጥናት እና ምርምር ሥራዎችን በጋራ ለመሥራት፤ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችን በማብቃት ለማሳደግ፤ ለዘርፉ ጠቃሚ የሆኑ የተቋማት ግንኙነቶች በማመቻቸት እንዲሁም በፈጠራ ሥራዎች ዙሪያ የተለያዩ ሁነቶችን በጋራ ለማዘጋጀት እንደሚረዳ ተገልጿል፡፡