“አድዋስ” በተሰኘው ቴአትር ላይ ዳሰሳዊ ውይይት ተካሄደ

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የሥነጥበባት ማዕከል በኅብረ-ተሳትፏዊ (‘‘ensemble’’) አቀራረብ ስልት በተዘጋጀውና “አድዋስ” በተሰኘው ቴአትር ላይ ዳሰሳዊ ውይይት ተካሄደ፡፡

በመራኼ ተውኔት ተስፋዬ እሸቱ የተዘጋጀውና በያሬድ ሹመቴ የተደረሰው ቴአትር በወዳጅነት አደባባይ ሲቀርብ የተሳተፉ እና ሌሎች ባለሙያዎች በውይይት መርሐ ግብሩ ዕለት ሙያዊ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የአካዳሚው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ ሳይንሳዊ እውቀትን ለማስፋፋት፣ ምርምሮችን ለማበረታታት እና ሳይንስን የባህሎቻችን አካል ለማድረግ ከሚጠቀምባቸው መንገዶች ሥነጥበብ አንዱ መሆኑን ጠቁመው አካዳሚው ይህንኑ ተግቶ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተውኔቱ አጠቃላይ ይዘት ላይ ሙያዊ አስተያየት የሰጡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል መምህርት ወ/ሮ ትዕግሥት አለማየሁ ታሪክ ቀመስ ተውኔቱ በአድዋ ድል ሚና የተጫወቱ ገፀ ባህርያትን፣ መቼቱን፣ ታሪኩን በመጥቀስና በተለይም በፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም ግለታሪክ “ኦቶባዮግራፊ” መጽሐፍ ላይ በመመሥረት፣ እንዲሁም የጉዞ አድዋ ገጠመኞችን በማስተሳሰር በሙዚቃዊ የአቀራረብ ስልት መቅረቡን ገልጸው ሙያዊ ትንታኔያቸውን አቅርበዋል፡፡

የውይይት ሐሳብ አቅራቢዋ ወ/ሮ ትዕግሥት ድርሰቱ ከተክለ ሐዋርያት ግለ ትረካ መነሳቱ በአድዋ ታሪክ ላይ ጉልህ ድርሻ ያላቸውን የእቴጌ ጣይቱ እና የንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ምኒልክን ሚና የሚያደበዝዝ ጥላ እንዳሳረፈበት አውስተው በቴአትር ዝግጅት እና ቴከኒክ ረገድ የተሻለ ጥረት እንደታየበት አብራርተዋል፡፡

የሙዚቃ ባለሙያው አቶ ሰርጸ ፍሬ ስብሐት በበኩላቸው፣ ቴአትሩ የቀደመውን የአድዋ ትውፊት በአዲስ መንፈስ ለመቃኘት፣ የአሁኗን ኢትዮጵያን በሚመስሉ የዳንስ እና የሰርከስ ትዕይንቶች የታጀበ፣ የአድዋን መንፈስ ከትናንት እያነሳ ከዛሬ እያዋሃደ ነገን በልኩ የማበጀት ሥራ መሆኑንና ሙዚቃውም ለጆሮ የሚጥም አቀራረብ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ቴአትሩ አንጋፋዎቹን ተዋንያን አበበ ባልቻ እና ተፈሪ ዓለሙን እና አዳዲስ ተተኪ ተዋንያንን፣ ዳንሰኞችን፣ የሰርከስ ባለሙያዎችን እና ሙዚቀኞችን ማሳተፉንና በርካታ ወጣት ተዋንያን ከአንጋፋዎቹ ልምድ መቅሰም እንዲችሉም እድል ለመፍጠር የተደረገውን ጥረትም አቶ ሰርጸ አድንቀዋል።

“ጉዞ አድዋ”  በሚል ፕሮጀክት ላለፉት 8 ዓመታት በየዓመቱ ከአዲስ አበባ እስከ አድዋ 1010 ኪሎ ሜትሮችን የሚሸፍን የእግር ጉዞ በማድረግ፣ የአድዋ ድል በዓልን በመዘከር፣ በትውልዱ ዘንድ ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኝ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ መቆየታቸውን የጠቀሱት የቴአትሩ ጸሐፊ አቶ ያሬድ ሹመቴ ለ126ኛው የአድዋ ድል በዓል ደግሞ “አድዋስ” የተሰኘ ታሪካዊና ዘመናዊ ሙዚቃዊ ተውኔት ለተመልካች ማቅረባቸውን ለተሳታፊዎች አብራርተዋል።

አክለውም በቴአትሩ ታሪክ የንጉሡ እና የንግሥቲቱ ሚና ለምን ደበዘዘ? ለሚለው ጥያቄ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ዘመናዊ ቴአትር አስፈንጣሪ ተደርገው የሚወሰዱት  ፊታውራሪ ተክለ ሐዋሪያት በትረካቸው እና ግለታሪካቸው የተናገሩትን ዋቢ በማድረግ የቀረበ መሆኑን በመግለጽ፣ ሆኖም በወቅታዊው ሀገራዊ ሁኔታ እና የጉዞ አድዋ ገጠመኝን ለማመላከት እና የትርጓሜያዊ አንድምታ ትስስር የሚፈጥር የትረካ አንጓ ሆኖ በመገኘቱ በመነሻነት መያዙን አብራርተዋል፡፡

በተውኔቱ ውስጥ የንግሥቲቱም ሆነ የንጉሡ ታሪክ ጎልቶ ያልወጣው በተውኔቱም ሆነ በጉዞው እንዲሁም ዛሬም ባለው ተጨባጭ ሁኔታ አድዋ ላይ አልደረስንም የሚለውን ትንታኔ ለመስጠት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

“አድዋስ” በተሰኘው በዚህ ታሪክ ቀመስ ቴአትር ለመግለጽ የተፈለገው ከ126 ዓመታት በፊት በተደረገ ጦርነት የተገኘ ድልን ብቻ ሳይሆን፤ ጀግኖቹን ለአድዋ ድል ያበቃቸውን የኢትዮጵያውያንን ታማኝነት፣ ጽናትና አንድነትን ለማጉላት እንደሆነ መራኼ ተውኔቱ  ተስፋዬ አብራርተዋል፡፡

የተውኔቱ ደራሲም የድርሰቱን ታሪክ፣ መራኼ ተውኔቱም እንደዚሁ ተውኔቱን የመራበትን አካሄድ እና የዝግጅት ታሪኩን በአጭሩ ለታዳሚዎች ገልጸዋል፡፡ ከታዳሚዎች ቀርበው ለነበሩ ጥያቄዎችም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በውይይቱ ማጠቃለያ የሳይንስ አካዳሚ የሥነ ጥበብ እንቅስቃሴዎች ላይ ሳይንሳዊ አበርክቶ ለማድረግ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ባለሙያዎቹ  ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የሥነጥበባት ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ይታገሱ ጌትነት ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር፣ ከባለሙያዎችና ከተመልካቾች በተሰጡት አስተያየቶች መሠረት ተውኔቱ በትልቅ አቅም ለሌሎችም እንዲደርስ ሃሳብ የሰጡ ሲሆን፤ በሌሎች ኪናዊና ባህል ተኮር የማዕከሉ እንቅስቃሴዎች ባለሙያዎች አብረው እንዲሠሩ ጋብዘው ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡