አካል ጉዳተኛ ከያንያንና አካል ጉዳተኝነት በኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ

በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሥር የሚገኘው የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነ ጥበባት ማዕከል በየ15 ቀኑ በሚያደርገው የጥበብ ውሎ 56ኛው ዝግጅት ቅዳሜ ሰኔ 22/2011 ዓ.ም ‹‹አካል ጉዳተኛ ከያንያንና አካል ጉዳተኝነት በኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ›› በተሰኘ ርዕስ አካሂዷል፡፡

በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሥር የሚገኘው የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነ ጥበባት ማዕከል በየ15 ቀኑ በሚያደርገው የጥበብ ውሎ 56ኛው ዝግጅት ቅዳሜ ሰኔ 22/2011 . ‹‹አካል ጉዳተኛ ከያንያንና አካል ጉዳተኝነት በኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ›› በተሰኘ ርዕስ አካሂዷል፡፡

በእለቱ የስነ-ልቦና መምህርት መቅደስ የአካል ጉዳት አይነቶች፣ የሚከሰቱባቸው መንገዶችና እንደ ማኅበረሰብ መወሰድ ስለሚገባው ሁሉን-አቀፍ እርምጃ ገለጻ ያቀረቡ ሲሆን፣ የሙዚቃ ባለሙያው አቶ ሠርፀ ፍሬስብሃት  የውይይት መነሻ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡

እንደ ሙዚቃ ባለሙያው ገለፃ አካል ጉዳተኝነትና ኪነጥበብ በዓለም ታሪክ ከፍተኛ ትስስር ያለው እንደሆነ ጠቅሰው ለአብነትም እነ ሆሜር፣ ሮኒ ሚልሳፕ፣ ስቲቪ ዎንደር፣ ሬይ ቻርለስ እና ሌሎችን ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያም የአይነ ስውራን ሙዚቃ በ1940 ዓም በስዊድን የቤሎናይት ሚሽነሪዎችት/ት ቤት ካዛንቺስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የተጀመረ ሲሆን አበራ ጉልላት እና ሌሎች ታላላቅ የሙዚቃ ሥራዎች የሠሩ ከመጀመሪያዎቹ ተማሪዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ተማሪዎቹም በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሙዚቃ ኦርኬስትራ ውስጥ ዕድሉን እያገኙ አገልግለዋል፡፡

ከዚያም የሰበታ አይነስውራን ትምህርት ቤት በ1950ዎቹ ተቋቁሞ ሥራውን ተረክቦ እስከአሁን እየሠራ ይገኛል። የሰበታ አይነስውራን ትምህርት ቤት አራት ሆስቴሎች ያሉት ሲሆን፣ እነሱም በታወቁ አይነስውራን ሙዚቀኞች ስም ተሰይመዋል።

በአይነስውራን ሙዚቀኞች፣ አቀናባሪዎችና የሙዚቃ ድረሰት አዘጋጆች ደረጃ የአይቤክስ ባንድ ሙዚቃ አቀናባሪው ኃይለማርያም ወልደጊወርጊስ ተጠቃሽ አይነስውር ሙዚቀኛ ነው። ተሾመ አሰግድም ድምጻዊ፣ ሙዚቃ ደራሲና ባልተለመደ መልኩ አይነስውር የሙዚቃ መሪም (ኮንዳክተር) ነበር። ተሾመ ከ1980 ወዲህ ከፍተኛ ዕውቅና ያተረፈ አቀናባሪ ነው።

ብርሃኔ ኪዳኔም የታሪክ ምሁር ሲሆን የሙዚቃን ታሪክ በመጻፍና ከትልልቅ ሙዚቀኞች ጋር በመሆን ተጠቃሽ ሥራዎችን በማቀናበር የሚታወቅ አይነስውር ሙዚቀኛ ነው። ከነዚህ በተጨማሪም በቅርቡም እነ ይትባረክ አባተና ይርዳው ጤናውን ማውሳት እንደሚቻል ቀርቧል።

የአይነስውራን ተሳትፎ በኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ዕድገት ውስጥ ትልቅ አስተዋፅዖ ያለው ቢሆንም፣ ባለሙያዎቹ ተገቢው ትኩረትና ድጋፍ እንዳልተሰጣቸው አቶ ሠርፀ ገልጸዋል፡፡

በጥበብ ውሎው እንግዳ የነበሩት ወ/ሮ የትነበርሽ ንጉሴም “ጥበብ የሁሉም መጠጊያ ናት፣ ጥበብ ሁላችንንም እንድታገለግለን ለአካል ጉዳተኛ ከያንያን ያልተቋረጠ ድጋፍ ያስፈልጋል” በማለት ከያንያን አካልጉዳተኞችን ትኩረት በመስጠት ሥራዎቻቸውንና ከያኒዎቹን ማስተዋወቅና ሥራዎቻውንና ሕይወታቸውን በተገቢው መንገድ መጻፍ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎችም አካል ጉዳተኞች በኪነ ጥበብ ዙሪያም ብቻ ሳይሆን በቤተ-ዕምነት የዕውቀት አባትነት፣ በማኅበረሰብ ዕድገት፣ በመንግስት አስተዳደርና በፖለቲካ ውሳኔ ሰጪነት ዙሪያ ተጠቃሽ አበርክቶት እነዳላቸው ስለሚታወቅ ተገቢው ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል፡፡

ቀጣዩ የሐምሌ 6/2011 ዓ.ም ዝግጅት በአካል ጉዳተኛ ሰዓሊያን እና የሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎች ዙሪያ እንደሆነ ማዕከሉ አሳውቋል፡፡ በዕለቱም የብላቴንጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነ ጥበባት ማዕከል ዳይሬክተር፣ ደራሲና የሥነ ጽሑፍና ፎክሎር ባለሙያ አቶ እንዳለጌታ ከበደ መነሻ ጽሁፍ እንደሚያቀርቡ ታውቋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *