አካል ጉዳተኛ ከያንያንና አካል ጉዳተኝነት በኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ

“የአካል ጉዳተኛ በመሆናችን የተለየ ድጋፍ አልጠየቅንም፤ ጥያቄያችን እንደማንኛውም የስነ ጥበብ ሰው ተስማሚ ምህዳር እንዲፈጠርና ስራዎቻችን ለኅብረተሰቡ ግምገማ እንዲቀርቡ ነው” ሠዓሊ ብሩክ የሽጥላ

በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሥር የሚገኘው የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነ ጥበባት ማዕከል በየ15 ቀኑ በሚያደርገው የጥበብ ውሎ 57ኛው ዝግጅት ዛሬ ሐምሌ 6/2011 . ‹‹አካል ጉዳተኛ ከያንያንና አካል ጉዳተኝነት በኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ›› በተሰኘ ርዕስ ከ56ኛው ውሎ የቀጠለ መርሐ-ግብሩን አካሂዷል፡፡

በዚህ ዝግጅት ሠዓሊ ብሩክ የሽጥላ እና የብላቴንጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነ ጥበባት ማዕከሉ ዳይሬክተር፣ ደራሲና የሥነ ጽሑፍና ፎክሎር ባለሙያ አቶ እንዳለጌታ ከበደ የውይይት መነሻ ሃሳብ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል፡፡

ሠዓሊ ብሩክ የሽጥላ ባቀረበው ንግግር በኪነጥበብ ውስጥ ያሉ ከያንያን አካባቢው፣ ሕብረተሰቡ ለአካ ጉዳተኛ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ያለው የተጓደለ አረዳድ እና የሥነ ጥበብ የኢንዱትሪው ሥርዓት የሚፈጥሩባቸው እክሎች አቅማቸውን በተገቢው እንዳይጠቀሙ እያደረጉ እንደሆነ ተናግሯል።

በተለይ የጥበብ ሥራን በትክክለኛው ጥበባዊ መመዘኛ በመመዘን ሥራው ላይ ማተኮር እና ከሀዘኔታ የመነጨ ድጋፍ ሊኖር ኤገባውም በማለት የገለጸው ሠዓሊ ብሩክ የአካል ጉዳተኛ በመሆናችን የተለየ ድጋፍ አልጠየቅንም፤ እንደማንኛውም የስነ ጥበብ ሰው ተስማሚ ምህዳር እንዲፈጠርና ስራዎቻችን ለኅብረተሰቡ ግምገማ እንዲቀርቡ ነው” ሲልም ድጋፋችን በተሠራው የጥበብ ሥራ ጥራትና ደረጃ ላይ እንጂ በአካል ጉዳቱ ላይ መመሥረት የለበትም ብሏል፡፡

ሠዓሊ ብሩክ የሽጥላ እስከ አሁን ድረስ ከ350-400 የሚሆኑ የሥዕል ስራዎች የሠራ ሲሆን 5  በግሉ 6 ደግሞ ከሌሎች ሠዓሊያን ጋር በጋራ የተዘጋጀ የሥዕል አውደ ርዕይ ለዕይታ አብቅቷል

ሌላው ‹‹በኢትዮጵያውያን አካል ጉዳተኛ ደራስያንና አካል ጉዳተኝነት በአማርኛ ሥነጽሑፍ›› በተሰኘ መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት ደራሲ፣ የሥነ ጽሑፍና ፎክሎር ባለሙያው አቶ እንዳለጌታ ከበደ ናቸው፡፡

1

አቶ እንዳለጌታ አካል ጉዳተኛ ደራስያን በዓለማችንአካል ጉዳተኝነት በአካል ጉዳተኛ ኢትዮጵያውያን ደራስያን እንዲሁም አካል ጉዳተኝነት በሌሎች ኢትዮጵያውያን ደራስያን በሚል ከፋፍለው አቅርበዋል፡፡

አካል ጉዳተኛ ደራስያንና አካል ጉዳተኝነት በዓለም የሥነጽሑፍ ክፍል ውስጥ የግሪኩ ሶፎክለስ ኦዲፐስ ንጉሥ፣ ማርጋሬት ሚሸልፌዮዶር ዶስቶቭስኪ፣ ፐርል በክማርሴል ፓኞል እና ሄለን ከለርን እንደምሳሌ ማሳት እንደሚቻል ቀርቧል፡፡

በኢትዮጵያም አካል ጉዳተኛ ደራስያን በተለይ በግዕዝ እና ነባር ሥነጽሑፍ ውስጥ እማሆይ ገላነሽ አዲሴ፣ ታላቁ ሊቅ አያሌው ታምሩ እንዲሁም መጋቢ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁ በስፋት እንደሚጠቀሱ አቶ እንዳለጌታ ተናግረዋል፡፡

በዘመናዊ የአማርኛ ሥነ-ጽሑፍ ውስጥ ደግሞ እነ ደበበ ሠይፉ (የብርሃን ፍቅር፣ ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ)፣ አውግቸው ተረፈ (ወይ አዲስ አበባ)፣ ቴዎድሮስ ጸጋዬ (ነፍሰጡር ስንኞች)፣ ኃይል ከበደ (ጉርሻና ፌሽታ)፣ ሠዓሊ ብሩክ የሺጥላ (የኔ ሥጦታ)፣ ትዕግስቱ ተክለማርያም (በርናባስ) ጎልተው የሚነሱ አካ ጉዳተኛ ደራስያን ናቸው፡፡

አካል ጉዳተኝነት በሌሎች ደራስያን ረጅም ልቦለዶች ውስጥ ደግሞ የሺጥላ ኮከብ (ወገግታ)፣  ገበየሁ አየለ (ዕንባና ሳቅ)፣ ወንድሙ ነጋሽ ደስታ (እንቡጥ ጽጌረዳ)፣ ዐቢይ አሕመድ (ፒኤች.)(ዲራአዝ) ሰተቴ፣ እንዳለጌታ ከበደ (እምቢታ፣ ያልተቀበልናቸው) የሚነሱ ሲሆን፣ በአጫጭር ልቦለዶች በኩል የጸጋ ዮሐንስ (ጦስ)፣ እና የበዕውቀቱ ሥዩም (ራትና መብራት) ተጠቃሽ ሥራዎች መሆን ይችላሉ ብለዋል አቅራቢው፡፡

በውይይት ወቅትም በበርካታ የኪነ ጥበብ ዘርፍ አካ ጉዳተኞች በአብዛኛው ራሳቸውን ለማኖር የሚቸገሩ ተደርገው መቅረባቸው መስተካከል ያለበት የተሳሳተ ግንዛቤ መሆኑ የተነሳ ሲሆን፤ የኪነጥበብ ታሪክ ጸሐፊዎችም ለቀጣዩ ትውልድ ኪነ-ጥበብን ታሪክ፣ ዕድገትና ፈተና እየመዘገቡ ማስቀመጥ እንዳለባቸው ተነስቷል፡፡

በዕለቱ የጥበብ ውሎ ዝግጅት የሙዚቃ ተመራማሪ ሠርፀ ፍሬስብሃትን ጨምሮ በርካታ ታዳሚዎች ተገኝተዋል፡፡ አካል ጉዳተኛ ወጣቶችም ግጥሞቻውን አቅርበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *