በዱር እንስሳት አያያዝና አጠቃቀም ዙሪያ ሳይንሳዊ ዘዴ ያስፈልገናል

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በአገሪቱ የዱር እንስሳት ሐብት አያያዝ፣ አጠቃቀም፣ ችግሮቹ እና የወደፊት መፍትሄዎቹ ላይ ያተኮረ ሳይንሳዊ ገለፃ አካሄደ፡፡

ዶ/ር አሰፋ መብራቴ

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በአገሪቱ የዱር እንስሳት ሐብት አያያዝ፣ አጠቃቀም፣ ችግሮቹ እና የወደፊት መፍትሄዎቹ ላይ ያተኮረ ሳይንሳዊ ገለፃ አካሄደ፡፡

ጥር 24/2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ግቢ በተካሄደው ውይይት የዕለቱ ገለፃ አቅራቢ ዶ/ር አሰፋ መብራቴ ኢትዮጵያ በዓለማችን ቀዳሚ 25 የብዝሃ-ሕይወት ክምችት ከሚገኝባቸው አገራት ውስጥ ትገኛለች፡፡ ይህ ብዝሃ-ሕይወት የተመሠረተው ልዩ በሆነው ተፈጥሯዊ መልክዓ-ምድር እና የዕፅዋት ክምችት ሲሆን በርካታ የዱር እንስሳት ሐብታችንም የዚሁ አካል ነው በማለት አብራርተዋል፡፡ አቅራቢው የዱር እንስሳት ሐብትንና አይነት (ዝርያን) በሚመለከት የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ  ባለሥልጣን መ/ቤት መረጃን ጠቅሰው እንዳከሉት፤  በአሁኑ ሰዓት ከ320 በላይ የአጥቢ ዱር እንስሳት ዝርያ ሲኖር፤ የአዕዋፍት ዝርያ ብዛት 862 እንዲሁም ከ240 በላይ በደረታቸው የሚሳቡ እንስሳት ሐብት ይገኛል፡፡ ከነዚህ ውስጥ 36ቱ የአጥቢ፣ 18ቱ የአዕዋፍት ዝርያ እንዲሁም 15ቱ ተሳቢ የዱር እንስሳት በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

በ1960ዎቹ በኢትዮጵያ እንስሳቱን ከጥፋት ለመታደግ የሚረዱ 5 ጥብቅ ቦታዎች ብቻ የነበሩ ሲሆን ከግማሽ ምዕተ-ዓመት በኋላ በሂደት 27 የደረሱ ሲሆን፤ ከአጠቃላይ የአገሪቱ የቆዳ ሽፋን ውስጥ 18.4 በመቶ የሚሆነው የመሬት ይዞታ ለዱር እንስሳት ጥበቃ (ፓርኮችን ጨምሮ) የተከለለ ቢሀንም የእንስሳት ሀብታችን እየተመናመነ እና ዝርያቸው አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የሳይንሳዊ ገለፃው አቅራቢ ዶ/ር አሰፋ ይገልፃሉ፡፡

ተሳታፊዎች

በዕለቱ ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያዎችና አስተያየቶች ተነስተው አቅራቢው ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በፓርኮች፣ መጠለያዎች እንዲሁም ባልተከለሉና ጥብቅ ባልሆኑ ቦታዎች ተሠራጭተው የሚገኙት እንስሳት ላይ መንግስት ጥበቃና ልማት እያደረገ ቢሆንም በዘርፉ ያለው ችግር ሰፊ በመሆኑ የሁሉንም ጥረትና ርብርብ እንደሚፈልግ ዶ/ር አሰፋ ጉዳዩን በጥልቀት አስረድተዋል፡፡

ተሳታፊዎች

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚም በአገራችን ስላለው የዱር እንስሳት ሐብት ስርጭት፣ አይነት እና ስብጥር፤ አሁን ያለበት ደረጃ፣ በአጠባበቅና አያያዝ እንዲሁም አጠቃቀም ላይ ያሉ ዘርፈ-ብዙ ችግሮችን ከመንግስት ጋር በትብብር በመለየትና በማጥናት ተቋማዊና ሳይንሳዊ መፍትሄዎች እንዲዘየዱ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

ውይይቱን ተጨማሪ ፎቶዎች ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሳይንሳዊ ገለፃና ውይት መድረክ የዓመቱን መርሐ-ግብር ለማግኘት እዚህ ይጫኑ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *