ሳይንስን ማሐዘብ (ማንም ሰው እንዲያውቀው ማድረግ) ለምን ያስፈልጋል?

ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ የሳይንስ ምንነትና ሳይንስን ማንም ሰው እንዲያውቀው ማድረግ ያለው ጠቀሜታ በሚል ርእስ አነቃቂ ገለጻ አድርገዋል

ሳይንስን ማሐዘብ (ሳይንስን ማንም ሰው እንዲያውቀው ማድረግ) ያለውን ጠቀሜታ ለማሳወቅ፣ ሳይንስ ጥቂት ልሂቃን የሚራቀቁበትና የተለያዩ ፈጠራዎችን የሚያወጡበት ብቻ ሳይሆን የኅብረተሰቡ ባሕል እንዲሆን ለማስቻል ወይም የሳይንሱን ማኅበረሰብ ከሰፊው ማኅበረሰብ ጋር ለማቀራረብ የሳይንስ አካዳሚው የሳይንስ ማእከል በአዳራሹ ባዘጋጀው አነቃቂ ሳይንሳዊ ገለጻ መድረክ ላይ ኤምሬተስ ፕሮፌሰር ሽብሩ ተገኝተው ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በገለጻ መርሐግብሩ ላይ የቀድሞ የአፍሪካ ሳይንስ አካዳሚ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ብርሃኑ አበጋዝ፣ የ152 ሀገራት የሳይንስ አካዳሚዎች ጥምረት (ኢንተር አካዳሚ ፓርትነርሺፕ) ጣምራ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ፣ የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ፣ ሌሎች አንጋፋ ተመራማሪዎች፣ የስነጽሑፍ ባለሙያዎች፣ የፕሮፌሰር ሽብሩ ቤተሰቦች፣ አድናቂዎችና ተማሪዎች ተሳትፈዋል።

ሳይንስን ማንም ሰው እንዲያውቀው የማድረግ ጠቀሜታው ብዙ ሲሆን ከሳይንሳዊ አስትሳሰብ የመነጨ እውቀት ተጨባጭና ተግባራዊ መሆኑን ጠቅሰው ሳይንስን ባህሉ ያደረገ ማኅበረሰብ ቶሎ ወደ ግጭት የማያመራ፣ ችግሮችን በውይይት የሚፈታና ሳይንስ አመክንዮአዊ እንደሚያደርግ ፕሮፌሰር ሽብሩ በገለጻቸው አብራርተዋል።

የሰው ልጅ ለሺህ ዓመታት ፀሐይን ቢያውቃትም ፀሐይ የጠፈር መሐል ለመሐል እንደምትገኝ ለመጀመርያ ጊዜ አሁን ካለው ሳይንሳዊ እውነታ ጋር ተቀራራቢነት ያለው መላምት ያስቀመጠው ፖላንዳዊው  ኒኮላስ ኮፐርኒከስ ሲሆን ጠፈር መሀለ ፀሐይ /Heliocentric/ እንደሆነና መሬትን ጨምሮ ሌሎች ፈለኮች /Planets/ በክብ ምህዋር ዙሪያ እንደሚዞሯት መላምቱን መስጠቱን ጠቅሰዋል። መላምቱም ከብዙ ክፍለ ዘመን በኋላ ተቀባይነት አግኝቶ በጀርመናዊው ዮሐንስ ኬፕለርና በጣሊያናዊው ጋሊሊዮ ጋሊሊ በአዲስ መልክ ተሻሽሎ አዲስ እውቀት ነባሩን እንደተካ የሳይንስን ሚና በምሳሌ አስደግፈው አብራርተዋል።

ፕሮፌሰር ሽብሩ ያቀረቡት ገለጻ፣ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የሰጧቸው ምላሾች ለሀገር የሚጠቅም እውቀት ያስጨበጡ ቢሆኑም መድረኩን ያላገኙ ብዙ ምሁራንና የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዳሉ ከመድረኩ ታዳሚዎች አንዳንዶች በሰጡት አስተያየት ቁጭታቸውን ገልጸዋል። ምሁራኑ እውቀታቸውን ለኅብረተሰቡ ለማዳረስ እንደዚህ ዓይነት መድረክ እንደሚያስፈልጋቸውም አሳስበዋል።

በርካታ ሰዎች እንደዚህ ዓይነት ሳይንሳዊ እውቀት ከሚያዳብሩ ስፍራዎች ይልቅ በመዝናኛ ላይ ስለሚያተኩሩ ለዜጎች የሚያስፈልጋቸው መዝናኛ ብቻ ሳይሆን ሳይንስን ጨምሮ መሬት ላይ ወርደው ብዙ ጠቀሜታ ሊሰጡ የሚችሉ ጉዳዮች ሊበረታቱ እንደሚገባም ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

የዚህን ገለጻ ሙሉ ቪዲዮ በቅርቡ በዩቲዩብ ቻናላችን እንዳሰራጨን በዚሁ እንደምናሳውቅ በአክብሮት እንገልጻለን።